Search

የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ቁጭት እና የትውልዱ ታሪካዊ አደራ

እሑድ ነሐሴ 24, 2018 109

የባሕር በር ማጣት የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ አደጋ ገና በጊዜ ከተነበዩ እና የውጭ ንግድ ሉዓላዊነት እሳቤን በምሁራዊ ብዕራቸው ካቀነቀኑ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ግንባር ቀደሙ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነት እና የባሕር በር ጥያቄ ከጂኦግራፊያዊ ዳርቻነት ባለፈ የሀገር ህልውና፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የሉዓላዊነት የደም ሥር መሆኑን ነጋድራስ ገብረሕይወት እጅግ በረቀቀ የምጣኔ ሀብት ትንታኔ አስቀምጠውታል። እርሳቸው ይህን የባሕር በር ጉዳይ ሲያነሱ በስሜት በመነዳት አልነበረም።

ይህ ጥልቅ ምልከታቸው የተቀረጸው ገና በልጅነታቸው ወደ ምጽዋ ካደረጉት ጉዞ ጀምሮ፣ በኋላም ባሕር አቋርጠው በአውሮፓ ባሳለፉት የትምህርት ዘመናቸው የዓለምን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጠንቅቀው በመረዳታቸው ነበር።

የስደት ሕይወታቸው የፈጠረላቸው ስፋት ያለው ዓለም አቀፋዊ ዕይታ በዘመኑ በሀገራችን የነበረውን ኋላቀር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት የመቀየርና ዘመናዊና ራሷን የቻለች ጠንካራ ኢትዮጵያን የመገንባት ጥልቅ ሕልም አሳድሮባቸዋል።

አውሮፓውያን በኢንዱስትሪ እና የባሕር በሮቻቸውን ተጠቅመው በዓለም ንግድ እንዴት እንደበለጸጉ በስደት ዘመናቸው በዓይናቸው ያዩት ገብረሕይወት፣ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ይህን አዲስ የለውጥ ሕልም እውን ለማድረግ እና ኢትዮጵያ ወደፊት ሊገጥማት የሚችለውን የጥገኝነት አደጋ ለማስቀረት ታላቅ ምሁራዊና ፖለቲካዊ ትግል ጀመሩ።

በዚህ ምክንያት የእርሳቸው ጥልቅ ምልከታ ዛሬም ድረስ ለትውልዱ እንደ መሪ ኮምፓስ ሆኖ ያገለግላል።

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ይህን የለውጥ ትግል ሲያፋፍሙ እና ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና መንግሥታዊ አስተዳደር ሲጽፉ ዘመኑ ለእርሳቸውም፣ ለሀገርም እጅግ ፈታኝ ነበር።

በወቅቱ ቀይ ባሕር እና ሰፊው የባሕር ጠረፋችን በጣሊያን ቁጥጥር ሥር ነበር። ይህን በኢትዮጵያ ላይ የተደረገ ሤራ፣ የስደት ዘመን ምልከታቸውን እና የለውጥ ራዕያቸውን በግልጽ ካሰፈሩባቸውና ዛሬም ድረስ በዋቢነት ከሚጠቀሱ ታላላቅ ምሁራዊ የጽሑፍ ማኅደሮቻቸው መካከል 1904 . የጻፉት "አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ" እንዲሁም 1916 . የታተመው ሥራቸው "መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር" ዋነኞቹ ናቸው።

በእነዚህ ድርሳኖቻቸው ውስጥ የጉምሩክ ሥርዓትን፣ የግብር አሰባሰብን እና የውጭ ንግድ ሚዛን መዛባትን በሳይንሳዊ መንገድ ሲተነትኑ፣ ከልባቸው የሚፈልቁ ሐሳቦች በሦስት ታላላቅ ማዕዘናት የተቃኙ ነበሩ፤ እነርሱም የታሪክ ትዝታ፣ ምሁራዊ ቁጭት እና የነገ ተስፋ ናቸው።

የነጋድራስ ገብረሕይወት ትዝታ፥ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ መድረክ እና የነፃነቷ መሠረት የነበረበትን፣ ሀገራችን በዓለም አቀፉ የንግድ መስመር ደማቅ አሻራ ያሳረፈችበትን ታላቁን የአክሱም ዘመን ሥልጣኔ የሚያስታውስ ጥልቅ ትዝታ ነበር።

ይህ የባሕር በር የንግድ መርከቦች የሚርመሰመሱበት እና ሀገራችን ከዓለም ጋር የምትገናኝበት የኢትዮጵያውያን መመኪያ የሆነ የወርቅ ድልድይ እንደነበር የታሪክ ማኅደር በማገላበጥ፣ ያን የከበረ የሉዓላዊነት ዘመን በናፍቆት ጭምር የዘከሩበት ነበር።

ከዚህ ደማቅ ታሪካዊ ትዝታ ጋር አብሮ የሚጓዘው ደግሞ በነጋድራስ ልብ ውስጥ ይብላላ የነበረው ጥልቅ ቁጭት ነው።

ታሪካዊ ጠረፍ የባዕዳን መፈንጫ ሲሆን መመልከት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ መተንፈሻ አጥታ በገዛ ባሕሯ ላይ የውጭ ኃይሎች ሲፈነጩ እና የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ በጉምሩክ ኬላዎቻቸው ሲቆጣጠሩት ማየት፣ እጅግ ጥልቅ የሆነ ምሁራዊ ንዴት አጭሮባቸዋል።

"መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር" መጽሐፋቸው ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ያመረቱትን ምርት ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ የውጭ ሸቀጥን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በባዕዳን ወደቦች ላይ ጥገኛ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያን የዘለዓለም የኢኮኖሚ ጥገኛ እንደሚያደርጋት በስደት ዘመናቸው ባገኙት የዓለም አቀፍ ንግድ ዕውቀት በሚገባ ተረድተው ነበር።

ሆኖም ከዚህ ሁሉ ቁጭት እና የታሪክ ትዝታ ባሻገር፣ ነጋድራስ የነበራቸው ተስፋ እጅግ ብሩህ እና ራዕያቸውም ወደፊት አሻግሮ የሚያይ ነበር።

የውጭ ካፒታልን አግልሎ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪን ለመገንባት እና የንግድ መዛባትን ለማስቀረት፣ የባሕር በር ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን አበክረው አስተምረዋል።

ነጋድራስ ይህን ታላቅ የኢኮኖሚ ራዕይ ሰንቀው ቢያልፉም፣ ከዓመታት በኋላ 1945 . በነጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ያላሰለሰ የዲፕሎማሲ ጥረት ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ስትቀላቀል እና ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ዳግም ስታስመልስ፣ በሕይወት ኖረው ይህን ታሪካዊ ክስተት ቢያዩ ኖሮ ምን ይሰማቸው ነበር?

ያለጥርጥር በውስጣቸው ይብላላ የነበረው ጥልቅ ቁጭት በታላቅ የድል እንባ ይተካ ነበር። በእነዚያ ድርሳኖቻቸው ያሰቡት የኢኮኖሚ ግንብ መሠረት ሲጣል፣ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እና የንግድ መርከቦች በገዛ ባሕራቸው ላይ ሲንሳፈፉ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ምጣኔ ሀብት በራሱ መተንፈሻ ሲያንሠራራ ቢመለከቱ፣ ልባቸው በታላቅ ሐሴት ይሞላ ነበር።

በስደት ዘመናቸው ያለሟት ሉዓላዊት እና የበለጸገች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የንግድ መስመር እኩል ተዋናይ ስትሆን ማየት ለእርሳቸው የሕይወታቸው ትልቁ ራዕይ ፍጻሜ በሆነ ነበር።

ይህን የነጋድራስ ገብረሕይወትን እሳቤ በዛሬው መረጃ እና በተጨባጭ ሀቆች ላይ ተመሥርተን ስንመረምረው፣ ኢትዮጵያ ዳግም ወደብ አልባ መሆኗ ያመጣው ኪሳራ እርሳቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ያስጠነቀቁት ትንቢት በተግባር መረጋገጡን ያሳያል።

በመጽሐፋቸው እንዳስቀመጡት ወደብ አልባ መሆን ማለት "ያልተመጣጠነ የውጭ ንግድ" እና የኢኮኖሚ ብዝበዛ ሰለባ መሆን ማለት ነው።

ይህ ሳይንሳዊ ሐሳብ ዛሬ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ እና ለሎጂስቲክስ ብቻ በየዓመቱ በምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተጨባጭ ሆኖ እናገኘዋለን።

ኢትዮጵያ ዛሬ በሎጂስቲክስ ወጪ ምክንያት በዓለም አቀፍ ገበያ ያላት ተወዳዳሪነት ሲዳከም፣ የነጋድራስ ገብረሕይወት ምሁራዊ ልዕልና እና የትንቢት ቃል ምን ያህል እርግጠኛ እንደነበር በቁጭት እንመሰክራለን።

የነጋድራስ ገብረሕይወት ቁጭት ወደ ተግባራዊ ተስፋ፣ ትዝታቸው ደግሞ ወደ ሕያው ታሪክ ሊቀየር የሚችለው፣ የዛሬው ትውልድ ይህን ራዕይ ዘመናዊ እና የተራቀቀ የስትራቴጂያዊ ግንኙነት ብልሀትን በመጠቀም ለማሳካት ሲተጋ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ከመቶ ዓመታት በፊት የዘሩት የኢኮኖሚ ነፃነት እና የሉዓላዊነት ዘር ነው።

ትውልዱ የነጋድራስን ቁጭት በመረዳት ያን ያጣውን የባሕር ጠረፍ በብልሃት፣ በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በማስመለስ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ደም ሥር የማነቃቃት ታሪካዊ ግዴታ አለበት።

የነጋድራስ ገብረሕይወትን ጥልቅ የኢኮኖሚ ፍልስፍና መሠረት በማድረግ ይህን የታሪክ አደራ ወደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማድረስ እና በመደመር እሳቤ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት፣ የአሁኑ ትውልድ በምን ዓይነት አዳዲስ የሚዲያና የዲፕሎማሲ ማዕቀፎች ላይ ቢያተኩር የተሻለ የውጤት ዐውድ መፍጠር ይችላል ብለው ያስባሉ? አስተያየትዎን ያስፍሩ።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: