በወላይታ ሶዶ ከተማ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም ዕለተ እሁድ 4 ሰዓት ገደማ ህጻን ልጅ አግተው በመውሰድ፤ ከወላጆቹ 1 ሚሊዮን ብር የጠየቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ አሰታወቀ።
በዕለቱ ህጻን ማሪና ዝናቡን ከመኖሪያ መንደሩ አግተው ከውሰዱ በኋላም፤ ወላጅ አባቱ ጋር በመደወል 1 ሚሊዮን ብር ዛሬውኑ ካልከፈልክ ልጅህን እገድለዋለን በማለት ሲያስፈራሩም እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።
አጋቾቹ 4 ግለሰቦች ህጻኑን አግተው ባቆዩበት መኖሪያ ቤት በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ ለኢቢሲ ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት ወንጀል በከተማዋ ያልተለመደ ነው ያሉት ኮማንደር ሀብታሙ፥ ሁሉም ቤተሰብ የህጻናትን ውሎ በአንክሮ በመከታተል ወንጀልን ቀድሞ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከህጻኑ ቤተሰብ ጥቆማ የደረሰው የሶዶ ከተማ ፖሊስ መምሪያም ከብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ጋር በመተባበር ህጻኑ ላይ ወንጀል ሳይፈጸም በመድረስ፤ ግለሰቦቹን እጅ ከፍንጅ መያዙን ያስታወቁት ደግሞ የሶዶ ከተማ ፖሊስ የመረጃ እንተሊጀንስ ዲቪዥን ኃላፊ ረ/ኢንስፔክተር እንግዳ ወርቁ ናቸው።
ግለሰቦቹ ህጻን ማሪናን ወደ ሌላ አካባቢ ለማሸሽ ሲሞክሩ እንደነበረም ጠቁመዋል።
ግለሰቦቹ በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደም ይገኛል ተብሏል።
በተመስገን ተስፋዬ