ለዘመናት ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነትን በደም እና አጥንታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያሸጋግሩት የኖሩት ታላቅ የክብር ካባ ነው። ይሁን እንጂ፣ በዘመናችን የሉዓላዊነት ትርጓሜ ከባህላዊው አውድ እጅግ የሰፋ ነው።
ዛሬ ላይ አንዲት ሀገር ሉዓላዊት ናት የምትባለው የራሷን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር፣ የዜጎቿን ደኅንነት የማረጋገጥ እና ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘሩባትን የፀጥታ ስጋቶች ከሥሩ የመመከት አስተማማኝ አቅም ስትገነባ ነው።
ለዚህ ደግሞ በማንኛውም መለኪያ ጠንካራ፣ የላቀ ሙያዊ ሥነ-ምግባር ያለው እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ የመከላከያ ኃይል መገንባት የሕልውና ጉዳይ ሆኗል።
ትናንት አባቶቻችን በጋሻ እና ጦር፣ በቆራጥነት የጠበቁት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ዛሬ ፈጽሞ የተለየ እና እጅግ ውስብስብ ወደሆነ የትግል ምኅዳር ተሸጋግሯል። የዛሬው የፀጥታ ስጋት ከባህላዊው የጦር ሜዳ ባሻገር ሰፊ እና ረቂቅ መልክ ይዟል።
በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት እንዳስተዋለችው፤ የሳይበር ጥቃቶች፣ ሀገርን ለማፍረስ ታቅደው የሚሠሩ የመረጃ ጦርነቶች፣ ድንበር ተሻጋሪ ሽብርተኝነት፣ እንዲሁም የውክልና ጦርነቶች ዋነኛ የፀጥታ ስጋቶች ሆነዋል።
እነዚህን የማይታዩ ነገር ግን እጅግ አውዳሚ የሆኑ ፈተናዎችን ለመመከት፤ የመከላከያ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በላይ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በረቀቀ ስትራቴጂ ሊታጠቁ ግድ ይላቸዋል።
ዘመናዊ መከላከያ በመሣሪያ ክምችት እና በሰው ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በሠራዊቱ አዕምሯዊ ብቃት፣ በሙያዊ ሥነ-ምግባር እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት በመላመድ አቅሙ የሚለካ ሆኗል።
ይህንን የዘመኑን ፈተና በሚገባ የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጠነከረ፣ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ እና በቴክኖሎጂ የዘመነ መከላከያ ሠራዊት በመገንባት ላይ ትገኛለች። የውስጥ አቅምን ከማጎልበት ጎን ለጎን፣ ሀገራችን ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር የምታደርገው የፀጥታ እና ወታደራዊ ትብብር ተቋማዊ አቅሟን ይበልጥ ለማጠናከር ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አለው።
በቅርቡ በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል የተካሄደው ውይይት የዚሁ እውነታ ጉልህ ማሳያ ነው። በውይይቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ወደ አዲስ እና የላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር መግባባት ላይ መደረሱ፣ ለሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት አዲስ እና ብሩህ ገጽታን የሚያላብስ ትልቅ እርምጃ ነው።
ይህ ወታደራዊ ትብብር በወረቀት ላይ ከሚሰፍር የቃላት ስምምነት የዘለለ ጥልቅ ትርጉም አለው። ትብብሩ በሥልጠና፣ በከፍተኛ የሙያ ልምድ ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን ጨምሮ በዘመናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ሰፊ በር የሚከፍት ነው።
የኢትዮጵያ ሠራዊት አሁን የደረሰበትን የተቋማዊ አቅም ግንባታ ደረጃ በተመለከተ፣ የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጅ የሰጡት ምስክርነት ዐቢይ ማሳያ ነው። እኚሁ አንጋፋ ዲፕሎማት እንዳስረገጡት፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም እና ቁመና፣ ለሁለቱ ሀገራት ቀጣይነት ላለው ስትራቴጂያዊ አጋርነት እጅግ ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸው የሀገራችንን ጂኦ-ፖለቲካዊ ክብደት በግልጽ ያሳያል።
በተለይም የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት በማይለየው እና አቋራጭ የሽብር ስጋቶች በበዙበት የአፍሪካ ቀንድ፣ የትኛውም ሀገር ደኅንነቱን እና ሰላሙን በተናጠል ማረጋገጥ አይችልም። የጎረቤት ሀገር ሲታመስ የራስን በር ማንኳኳቱ አይቀርም። በዚህ አውድ ኢትዮጵያ የቀጣናው የሰላም መልሕቅ ሆና ታገለግላለች።
በመሆኑም የሀገራችን እና የአሜሪካ የፀጥታ ትብብር መጎልበት፤ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር፣ በቀጣናው ላይ ለሚታሰበው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
የዘመኑ የመከላከያ ተልዕኮ ዘርፈ ብዙ ነው። ሉዓላዊነትን በጽናት መጠበቅ፣ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ረቂቅ እና ዘመናዊ የፀጥታ ስጋቶችን ቀድሞ መመከት እንዲሁም ለሀገር ልማት እና ብልጽግና የሚያስፈልገውን ዘላቂ ሰላም መፍጠር ዋነኛ ግቦቹ ናቸው።
በዚህ ፈታኝ እና ወሳኝ ሂደት ውስጥ እያጎለበትን የመጣነውን ጠንካራ ሀገራዊ የመከላከያ አቅም፣ ከስትራቴጂያዊ የዓለም አቀፍ ትብብር ጋር አዋህዶ መጓዝ የዘመኑን ሁለገብ የፀጥታ ፈተናዎች ለመሻገር ብቸኛው እና አስተማማኙ መንገድ ነው!
በኢንትሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: