የኢትዮጵያ እግር ኳስ በአፍሪካ መድረክ የነገሠበት፣ ሰንደቅ ዓላማዋ በአኅጉሪቱ ትልቁ የስፖርት መድረክ ላይ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት ብሎም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምታልም ሳትሆን የዋንጫው ባለቤት የነበረችበት ወርቃማ የታሪክ ምዕራፍ ነበር።
ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም አዲስ አበባ የአፍሪካ እግር ኳስ መናኸሪያ ሆና 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታስተናግድ፣ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ለፍጻሜው ደረሰች። በኢትዮጵያ እና በታሪካዊው ድል መካከል የቆመው ደግሞ የወቅቱ ሻምፒዮን የነበረው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ነበር።
በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ስታዲየም (የአሁኑ አዲስ አበባ ስታዲየም) የተሰበሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቁን ድንቅ ምዕራፍ ለመመልከት ታደሙ። ፍልሚያው ግን እጅግ ፈታኝ ነበር።
በ35ኛው ደቂቃ ባዳዊ አብደል ፈታሕ ግብ አስቆጥሮ ግብጾችን መሪ አደረገ። በሁለተኛው አጋማሽ ግርማ ተክሌ አቻ ቢያደርግም፣ ባዳዊ በ75ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግቡን በማስቆጠር ኢትዮጵያን ከሽንፈት አፋፍ ላይ አድርሷት ነበር። ሆኖም 84ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈርጥ መንግሥቱ ወርቁ ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2 ለ 2 ተጠናቅቆ ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ አመራ።
በጭማሪው ሰዓት የታሪክ ገጾች ለኢትዮጵያ በደማቁ ተጻፉ። በ101ኛው ደቂቃ ኢታሎ ቫሳሎ ኢትዮጵያን መሪ ሲያደርግ፣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መንግሥቱ ወርቁ ለራሱ ሁለተኛዋን ግብ በማስቆጠር ውጤቱን 4 ለ 2 አደረገው። የዳኛው የመጨረሻ ፊሽካ ሲሰማ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኗ ታወጀ።
በዕለቱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የነበረው ደስታ እና ሕዝቡ በሬዲዮ ዙሪያ ተሰብስቦ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይከታተልበት የነበረው ስሜት ወደር አልነበረውም።
ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዋንጫውን ለአንበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ ሲያስረክቡ የታየው ምሥል የሀገር ብሔራዊ ኩራት መገለጫ ሆኖ ለትውልድ ተላልፏል።
ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የ1949ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ፣ በ1951ዱ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ካጠናቀቀች በኋላ ነው በ1954ቱ በግማሽ ፍጻሜው ቱኒዚያን 4 ለ 2 እንዲሁም በፍጻሜው ግብጽን በተመሳሳይ 4 ለ 2 በማሸነፍ በሁለት ጨዋታዎች 8 ግቦችን አስቆጥራ ታሪካዊውን ዋንጫ ወደ ቤቷ ያስገባችው።
ያ ድል ለሀገራቸን ከ64 ዓመታት በኋላ ዛሬም ድረስ ብቸኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሆኖ ይገኛል። የእግር ኳስ ዓለም ተቀይሯል፤ ውድድሩም በገንዘብ፣ በስታዲየሞች ደረጃ እና በታክቲክ እጅግ የበለጸገ ሆኗል።
ነገር ግን የመንግሥቱ ወርቁ፣ የሉቺያኖ ቫሳሎ፣ የኢታሎ ቫሳሎ እና የግርማ ተክሌ አሻራ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ሕያው ሆኖ ይኖራል።
ዛሬ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ዳግም ለማስተናገድ እና ወደ አኅጉሩ የውድድር መድረክ በድምቀት ለመመለስ በምታልምበት ወቅት፣ ይህንን ታሪካዊ ድል ማስታወስ ለወደፊቱ ጉዞ ትልቅ ብርታት ነው።
ምክንያቱም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ማማ ላይ ነበር፤ ሀገራችን ዋንጫውንም አሸንፋለች።
በመሆኑም ወደፊት የአፍሪካ መድረክ ላይ ስኬታማ ለመሆን የሚደረገው ጥረት የነገ ሕልም ብቻ ሳይሆን፣ ትናንት በተግባር የተረጋገጠ የታሪክ እውነት ጭምር ነው።
በእሱባለው ተሾመ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: