ለዘመናት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የሀገራችን ስም ሲነሣ አብሮ የሚታወሰው የድርቅ፣ የዕርዳታ ጠባቂነት እና "አትችልም" የሚል ትርክት ነበር።
"ኢትዮጵያ ዕምቅ አቅም እና የተፈጥሮ ጸጋ አላት" ቢባልም፣ ያንን የተቆለፈ አቅም በተጨባጭ መሬት ላይ አውርዶ ማሳየት የዘመናት ፈተናችን ሆኖ ዘልቋል።
ዛሬ ግን ይህ የረዥም ጊዜ የታሪክ ገጽ ተዘግቷል። ሀገራችን ተስፋን ወደ ተግባር፣ ራዕይን ወደ መሬት በማውረድ እውነተኛ አቅሟን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያችን እየታዩ ያሉ ሀገር በቀል የልማት ሥራዎች እና ግዙፍ የሜጋ ፕሮጀክቶች መሳካት፣ ሀገራችን ያላትን እውነተኛ አቅም እና የሕዝቧን የማስፈጸም ብቃት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ኢትዮጵያውያን ይችላሉ፤ ኢትዮጵያ ትችላለች፤ አቅሙ አለ፣ ብቃቱ አለ፣ ዕውቀቱ አለ፤ መተጋገዝ፣ መደጋገፍ እና አብሮ መቆም ከተቻለ ብዙውን ነገር ማሳካት ይቻላል” የሚለው ተደጋጋሚ ንግግር የዚሁ ተግባራዊ እውነታ ማጠንጠኛ ነው።
ይህ አባባል በቃል የሚነገር ብቻ ሳይሆን በየመንገዱ፣ በየማሳው እና በየግንባታው ስፍራ በገዛ ዐይናችን የምናየው እና በእጃችን የምንዳስሰው ሕያው እውነታ ሆኗል።
ይህንን ሀገራዊ እመርታ ለመረዳት ዙሪያችንን መመልከት በቂ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውጭ የጂኦ-ፖለቲካ ጫናዎችን እና የፋይናንስ ማዕቀቦችን በጽናት ተቋቁሞ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ መድረሱ፣ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እና ተደጋግፈው ከቆሙ የገንዘብም ሆነ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ እንደማያስቆማቸው ያረጋገጠ ኩሩ ሐውልታችን ነው።
በራሳችን አቅም እና ጥረት የተገነባው ይህ ፕሮጀክት "ሀገራዊ ሕልምን ማሳካት ይቻላል" ለሚለው ታላቅ ማስተማሪያ ነው።
ከዚህም ባሻገር ታሪክን የቀየረ ተግባር የታየው በግብርናው ዘርፍ ነው። የስንዴ እርዳታን ከባሕር ማዶ ትጠብቅ የነበረችው ሀገር፣ ዛሬ ላይ በበጋ ስንዴ ልማት ራሷን ችላ ለውጭ ገበያ (ኤክስፖርት) ምርት ማቅረብ ወደምትችልበት ታሪካዊ ምዕራፍ ተሸጋግራለች። ከ'ሌማት ትሩፋት' መርሐ ግብር ጋር ተዳምሮ ይህ ስኬት፣ ኢትዮጵያውያን "በራሳችን አቅም እና ዕውቀት ራሳችንን መመገብ እንችላለን" የሚለውን የምግብ ሉዓላዊነት በተግባር ያሳየበት ነው።
በሌላ በኩል በከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት፣ ለኢትዮጵያ አዲስ የሥራ ባሕልን ይዞ መጥቷል። ሌት ተቀን በማይቋረጥ ትጋት፣ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እና በፍጥነት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ማድረግ እንደሚቻል የኮሪደር ልማቱ በተግባር አሳይቷል።
"የመንግሥት ፕሮጀክት አያልቅም" የሚለውን አሮጌ አመለካከት በመስበር ያመጣው ይህ "በጊዜ ገደብ እና በጥራት የመሥራት" ዘመናዊ አቅም፤ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ እንዲሁም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በቴክኖሎጂው ዘርፍም በስፋት እየተደገመ ይገኛል።
እጅግ የሚያስደንቀው ደግሞ፣ እነዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የተከናወኑት ፈተናዎች በሌሉበት አልጋ በአልጋ በሆነ ምኅዳር ውስጥ አለመሆኑ ነው። ሀገራችን ከባድ የሰው ሠራሽ ጸጥታ ፈተናዎችን፣ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎችን እና የተፈጥሮ አደጋዎችን እያስተናገደች፣ በአንድ እጅ እምቧይ እያረመች በሌላ እጅ ማማ እየገነባች ያመጣቻቸው ድሎች መሆናቸው አቅማችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያመላክታል።
የልማት ሥራዎቹ ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት በዋነኝነት የዜጎች ዕውቀት እና ጉልበት ሲቀናጅ፣ እንዲሁም ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት ሲፈጠር መሆኑን ያለፉት ዓመታት አስተምረውናል።
አሁን የተጀመሩት የተቀናጁ የልማት እንቅስቃሴዎች እና የሕዝብ ትብብሮች ተጠናክረው ከቀጠሉ፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አፍሪካ አኅጉር ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ያላት መሪ ሀገር ሆና የመውጣት ሰፊ እና እርግጠኛ ዕድል አላት። አዎ፣ በተግባር እንደታየው ኢትዮጵያ ትችላለች!
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: