ከተሞች የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ሕይወት እና የዘመናዊነት መስታወቶች ናቸው።
የአንድ ከተማ ዕድገት በተገነቡ ሕንፃዎች፣ በተስፋፉ መንገዶች እና በተጨመሩ የንግድ ማዕከላት ብዛት ብቻ አይለካም።
እውነተኛ የከተማ ልማት የሚገለጸው ነዋሪዎች ንጹህ፣ አረንጓዴ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ለኑሮ ምቹ በሆነ አካባቢ መኖር ሲችሉ ነው።
አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገች ያለች የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ፣ ይህን ዕድገቷን ከሥነ-ምህዳር ጥበቃ እና ከሕዝብ ምቾት ጋር ማጣጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው።
በዚህ መነሻ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ከመንገድ ግንባታ ባሻገር የመዲናዋን ገጽታ እና የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል ያለመ ሰፊ የከተማ ለውጥ አቅጣጫ ሆኖ በትግበራ ላይ ይገኛል።
የከተማ ውበት በሰው ሠራሽ ግንባታዎች ብቻ አይፈጠርም፤ ዛፎች፣ መናፈሻዎች፣ ክፍት ቦታዎች እና የወንዝ ዳርቻዎችም የከተማዋ ተፈጥሯዊ ውበት ናቸው።
እነዚህ አረንጓዴ ስፍራዎች ለነዋሪዎች መዝናኛ እና ማረፊያ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ለከተማዋ ንጹህ አየር እና የተሻለ ከባቢን ይፈጥራሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ቦታዎችን መጠበቅ፣ ቆሻሻን በአግባቡ መያዝ እና ንብረቶችን መንከባከብም የከተማ ስልጣኔን የሚያሳዩ ተግባራት ናቸው።
ይህ ኃላፊነት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ነዋሪ የውዴታ ግዴታ ነው።
የከተማ ልማት ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ ከተማን መገንባት ነው።
በዚህ ረገድ አካል ጉዳተኞችን ጭምር ታሳቢ ያደረጉ ሰፊ እና ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መሄጃዎች እና የሕዝብ መዝናኛዎች የመዲናዋ ልማት ሰውን ያማከለ እንዲሆን አድርገዋል።
ይህ የልማት አቅጣጫ የመደመር እሳቤን በተግባር ያሳየ ሕያው ምስክር ነው። ልማትን ከሥነ-ምህዳርን፣ ዘመናዊነትን ከታሪክ፣ የመንግሥትን ሚና ከነዋሪዎች ተሳትፎ ጋር በማስተሳሰር የተሟላ የከተማ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
በዚህ መልኩ የኮሪደር ልማቱ ከመንገድ እና ሕንፃ ግንባታ ባሻገር ሰውን፣ ተፈጥሮን እና ልማትን በአንድ ማዕቀፍ የማበልፀግ ውጤታማ አቅጣጫን ተከትሏል።
የአዲስ አበባ የነገ ገጽታ ዛሬ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ይወሰናል። ዛሬ የሚተከሉ ዛፎች፣ የሚጠበቁ የተፈጥሮ ሀብቶች እና የሚገነቡ ሰው-ተኮር መሠረተ ልማቶች ለትውልድ የሚተላለፉ ዘላቂ የከተማ ቅርሶች ናቸው።
አዲስ አበባን ማልማት ማለት የሕንፃዎችን እና የመንገዶችን ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን፤ ተፈጥሮን የምትጠብቅ እና ለኑሮ የምትመች ጽዱ ዘመናዊት ከተማን መገንባት ማለት ነው።
ንጹህ፣ አረንጓዴ እና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነች ዘመናዊት አዲስ አበባን እውን ማድረግ ደግሞ ከከተማ ውበት ባሻገር የትውልዶች የተሻለ ሕይወት እና የዘላቂ ልማት ተስፋ ጉዳይ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: