Search

"ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ተነጋግረን መፍታት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ታሪካዊ መድረክ ነው" - የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 107

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ 2019 አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ይዞት የመጣውን ብሩሕ ተስፋ በተመለከተ ከኢቲቪ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም 4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የመከሩበት ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ሂደቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ስለሚኖረው በጎ ተፅዕኖ አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በባህሪው ልዩ እና ሕዝብ በባለቤትነት የመራው ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

መንግሥት ምቹ አውድ እና ገለልተኛ ተቋም ከመፍጠር በቀር በሂደቱ የነበረው ሚና የተሳታፊነት ብቻ ነው።

ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ የዘለቀው ሂደት ከአንድ ወር በላይ በፈጀ የማጠቃለያ ጉባኤ ተቋጭቷል።

4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በማካተት በአዲስ አበባ የተካሄደው ይህ የማጠቃለያ ጉባኤ ታሪካዊ ስኬት የተመዘገበበት ነው።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ምክክሩ በኢትዮጵያ ሲሰራበት የቆየውን "አሸናፊና ተሸናፊ" የዜሮ ድምር ፖለቲካ ልምምድ በመቀየር፣ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የጨዋታ ሕግ መፍጠር ችሏል።

በተለይም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው አካላት በአንድ የሰላም መድረክ ተሰባስበው በመነጋገር እና በመደማመጥ አንድ የሚያደርጋቸውን የጋራ መንገድ መፈለግ መጀመራቸው የስልጡን ፖለቲካ መገለጫ ነው።

በምክክሩ ወቅት 99 በመቶ በሚሆኑ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠሩ፣ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት እንደማይችሉ ይናፈሱ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ያመከነ ነው።

ሂደቱ ኢትዮጵያ በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ልምምድን ለማጽናት ያላትን ቁርጠኝነት ለወዳጅም፣ ለጠላትም ያሳየችበት ታላቅ ድል ነው።

የመደመር እሳቤ አንዱን አቅፎ ሌላውን ከማግለል ይልቅ የሁሉንም አቅም በማስተባበር ሀገር እና ሕዝብ አሸናፊ የሚሆኑበትን ሥርዓት መገንባት እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ሀገራችን የሚያስፈልጋት ሁሉንም አካታች የሆነ "የመግባባት ዴሞክራሲ" ነው ብለዋል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል ሰላምን ማጽናት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች እና የመላው ሕዝብ የጋራ ኃላፊነት ስለመሆኑ ቃል ኪዳናችንን በማደስ እንደሚገባም የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: