Search

የአኅጉራችን እውነተኛ ገጽታ እና የኢትዮጵያውያን አዲስ ዋዜማ፦ የተባበሩት መንግሥታት ታሪካዊው የዓለም ካርታ ማሻሻያ ውሳኔ

ቅዳሜ ነሐሴ 30, 2018 32

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካን አኅጉር እውነተኛ የመሬት ስፋት እና ገጽታ የሚያሳይ አዲስ የዓለም ካርታ ለመጠቀም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በከፍተኛ ድጋፍ አጽድቋል።

ቶጎ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የመራችው እና 164 ሀገራት የደገፉት ይህ ታሪካዊ ውሳኔ፣ ላለፉት አምስት ክፍለ ዘመናት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውን እና የአፍሪካን ስፋት አነስተኛ አድርጎ ሲያሳይ የነበረውን ነባሩን መርኬተር ካርታ በማስወገድ በምትኩ ትክክለኛውን ስፋት የሚያሳየውን Equal Earth የተሰኘውን የካርታ ንድፍ እንዲተካ ያደርጋል።

ነባሩ አሠራር አፍሪካን ከዴንማርኳ ግሪንላንድ ጋር እኩል አድርጎ ሲሥል የነበረ ቢሆንም በእውነታው ግን አኅጉራችን ከግሪንላንድ 14 እጥፍ የምትበልጥ እና ግዙፏን አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ጃፓንን እና አብዛኛውን የአውሮፓ ክፍል በውስጧ አቅፋ ይዛ ተጨማሪ ሰፊ መሬት የሚተርፋት ግዙፍ አኅጉር ናት።

ይህ በካርታ ላይ የተደረገ ታሪካዊ የእውነት ማስተካከያ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባትን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስፍራ የሚያበስር ታላቅ የዕውቅና ምዕራፍ ነው።

ይህ የእውነት ብስራት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ወደ አዲሱ ዘመን ለመሸጋገር በሚዘጋጁበት እና የአዲስ ዓመት ዋዜማቸውን በሚያደምቁበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ መከሰቱ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።

አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋን እና አዲስ ገጽታን ይዞ እንደሚመጣ ሁሉ ይህ የካርታ መስተካከልም አኅጉራችን እና ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እውነተኛ ገጽታቸውን እና ግዙፍ አቅማቸውን የሚያሳዩበት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ያበስራል።

ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዘመን በተስፋ፣ በሥራ እና በአዲስ መንፈስ እንደሚቀበሉት ሁሉ፣ አፍሪካም በራሷ ልጆች ጥረት እና እውነት የተሳሳቱ ታሪኮችን በማረም ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች እና የተከበረች አኅጉርን ለማስረከብ በጽኑ መሠረት ላይ ቆማለች።

በጌቱ ላቀው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: