ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምረቃት መልዕክታቸው ይፋ ያደረጉት "የማንሠራራት ዘመን" ጽንሰ ሐሳብ ዛሬ በ2018 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ ሆነን ስንገመግመው የኢትዮጵያን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እና የተግባር ከፍታ በግልጽ የሚያሳይ ብሩህ እውነት ሆኗል።
ይህ ታሪካዊ ራዕይ የፈተናው ዘመን ተሸኝቶ አዲስ ብሩህ ምዕራፍ መከፈቱን ያበሰረ ሲሆን፣ ፍልስፍናውም በጊዜ አጠቃቀም፣ በተጋድሎ እና በሕልውና ጽናት ላይ የተገነባ ነው።
ዛሬ የተሰኘችው ጊዜ፣ በፈተና በሞላው ትናንት እና በተስፋ በሚጠበቀው ነገ መካከል ያለች ወሳኝ የድርጊት ድልድይ መሆኗን ጥልቅ በሆነ መንገድ ያስገነዝባል።
አቴና፣ ሱሜር፣ ባቢሎን እና ሮም የመሳሰሉ ታላላቅ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች የዛሬን የትጋት ተጋድሎ በመዘንጋታቸው ታሪካዊ ክብራቸውን እንዳጡ ሁሉ የኢትዮጵያ መጻኢ ዕድልም የሚወሰነው በዛሬ ጽናት እንጂ በትናንት ትዝታ ብቻ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰፊው ማብራራታቸው ይታወሳል።
ይህ የማንሠራራት ዘመን በድንገት የመጣ ክስተት ሳይሆን፣ ቀደም ብለው በተጣሉ ጠንካራ መዋቅራዊ መሠረቶች ላይ የቆመ ነው።
ብሔራዊ የጥራት መንደርን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማዊ አቅሞች መገንባታቸው የዚህ ጥልቀት ያለው እውነት ማሳያ ነው።
በዚህ የተግባር ዘመን ውስጥ ከተመዘገቡት ታላላቅ ድሎች መካከል በኢትዮጵያ የመፈጸም ታሪክ ወደር የማይገኝለት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ መግባቱ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያን በዓለም 17ኛዋ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል።
ከዚህ ታላቅ የኃይል ፕሮጀክት በተጓዳኝ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የኦጋዴን ካሉብ ፕሮጀክት በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት አቅም መፍጠሩ፣ የጎዴ ከተማን ከድንበር ጠባቂነት ወደ ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት አሸጋግሮታል።
የማንሠራራት ዘመኑ ሌላኛው ትልቅ ተጨባጭ ስኬት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ታሪካዊ ድል ነው። ኢትዮጵያ በበጋ ስንዴ ልማት ባደረገችው ርብርብ የውስጥ ፍጆታዋን በመሸፈን ራስን ከመቻል አልፋ የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ የተሰበረውን ሥነ-ልቦና የጠገነ ታላቅ እመርታ ነው።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት ደግሞ የከተሞችን ገጽታ በዘመናዊ መንገድ የቀየረ እና ለዘመናት የነበረውን አሠራር የሰበረ ማሳያ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ445 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት የተከናወነ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ከዕሳቤ ተነስተው በመሬት ላይ የተረጋገጡ፣ የትራፊክ ፍሰትን በእጅጉ ያፋጠኑ፣ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እና የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ያሻሻሉ እውነተኛ ለውጦች ናቸው።
በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ መሠረት ለመጣል የተወሰዱት የሪፎርም ዕርምጃዎች ዘላቂ የፋይናንስ መረጋጋትን እያረጋገጡ ይገኛሉ።
ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያለው የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ መቋቋሙ ትልቅ የኢኮኖሚ ክስተት ነው።
ይህ ተቋም በባንክ ዘርፉ የነበረውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ችግር የሚፈታ ከመሆኑም በላይ፣ ለዜጎች ሰፊ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ዕድልን የከፈተ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መስከረም 2018 ዓ.ም የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ፣ መንግሥት የዜጎችን የመግዛት አቅም ለማጠናከር እና የኑሮ ጫናን ለማቃለል የያዘው ስትራቴጂያዊ ዕርምጃ አካል ሆኖ ተመዝግቧል።
በዲፕሎማሲው እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ የማንሠራራት ዘመኑ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተሰሚነት ማሳያ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም አኳያ የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ስምንት ዓመታት 56 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል፣ ኢትዮጵያ ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል።
የአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው 'መሶብ' የተሰኘው ዲጂታል መተግበሪያ ለአገልግሎት መብቃቱ የዲጂታል ኢኮኖሚው ስኬት ሲሆን፣ ዘመናዊ እና ቴክኖሎጂ የታጠቀ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱ ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አስተማማኝ ሰላም አስተማማኝ መሠረት ላይ ጥሎታል።
በአጠቃላይ ይህ የማንሠራራት ዘመን ከእጅ አዙር ጥገኝነት እና ከችግር ተቀባይነት ወደ ቀጠናዊ ኃያልነት የተደረገ የተግባር ሽግግር ነው።
ኢትዮጵያ የውስጥ አቅሟን አሟጦ በመጠቀም ብልጽግናዋን የምታረጋግጥበት መጻኢ ተስፋዋ እጅግ ብሩህ መሆኑን እኚህ ተጨባጭ ድሎች በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣሉ።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: