በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የኢንዱስትሪውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማነቃቃት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ለመሳብ እና የዜጎችን የቴክኖሎጂ ክህሎት ለማዳበር ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው አሠራር ፓርኮቹ በዋናነት ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደረገ እና የውጭ ባለሀብቶች ላይ የተንተራሰ ነበር።
ሆኖም ይህ አካሄድ ከውጭ ገበያ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም አቅምን የሚፈታተን በመሆኑ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ያካተተ ጠንካራ የኢንዱስትሪ መሠረት የመጣል አስፈላጊነት ታምኖበት ስትራቴጂያዊ የፖሊሲ ሽግግር ተደርጓል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማሸጋገሩ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት እንዲገቡ ማድረጉ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚያጸና እርምጃ ነው።
የሀገር ውስጥ አምራቾች ወደ እነዚህ ዞኖች መግባታቸው አስተማማኝ የመብራት፣ የውኃ፣ የቴሌኮም እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በአንድ ቋት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።
በተጨማሪም የንግድ ፈቃድ፣ የታክስ፣ የጉምሩክ እና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት የማግኘት እድል በመፈጠሩ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ አሰልቺ የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶችን በማስቀረት በአጭር ጊዜ ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ እና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል።
ከዓለም አቀፍ አምራቾች ጎን ለጎን መሥራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የዘመናዊ አሠራር፣ የአመራር፣ የጥራት ቁጥጥር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለቤት እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል።
ይህ ተሳትፎ ለውጭ ኩባንያዎች የሚሆኑ አጋዥ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት፣ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት አቅምን ያጎለብታል።
ይህም በከፍተኛ ሁኔታ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን፣ የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከር እና ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ድርሻ አለው።
የሀገር ውስጥ አምራቾችን ተሳትፎ ለማበረታታት ኮርፖሬሽኑ ተጨባጭ የድጋፍ ማዕቀፎችን ዘርግቷል።
ከአነስተኛ እና ጥቃቅን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ጥረት ለሚያደርጉ አምራቾች ለተወሰነ ጊዜ የሚሆን የለማ መሬት በነጻ የሚያገኙበት አሠራር ተመቻችቷል።
ከዚህም ባሻገር የምርት ተወዳዳሪነታቸውን ለማረጋገጥ የሚከፍሉት የሊዝ ክፍያ ከትላልቅ የውጭ ኢንዱስትሪዎች አነስተኛ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ውጤታማ አምራቾች በፍጥነት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ይገኛል።
ሆኖም የሀገር ውስጥ አምራቾች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ዘላቂ እና ፍሬያማ ይሆን ዘንድ የማሽነሪ ተከላ እና የካፒታል አቅምን የሚደግፉ የታለሙ የፋይናንስ አሠራሮች ሊጠናከሩ ይገባል።
ተደራሽ የሆኑ የረጅም ጊዜ ብድሮች፣ የሊዝ ፋይናንሲንግ፣ የብድር ዋስትና አሠራሮች እና ለጥሬ ዕቃና መለዋወጫ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ እንዲሁም በውጭ እና በሀገር ውስጥ አምራቾች መካከል የንግድ ትስስር እንዲፈጠር የሚያስገድዱ የፖሊሲ ማዕቀፎችን መተግበር የዘርፉን ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።
ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የውጭ ኢንቨስትመንት መሳቢያ ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾች አቅም መገንቢያ ማዕከላት አድርጎ መስራት የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ መሠረት ያጠናክራል።
ይህ የተቀናጀ አካሄድ የወጪ ንግድን ከመደገፍ ባሻገር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጽናትን በመገንባት ለዘላቂ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: