Search

ከውጭ ምንዛሪ እጥረት አዙሪት ወደ አስተማማኝ አቅርቦት

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 21

በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ለዓመታት ትልቅ ማነቆ የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተወሰዱ መዋቅራዊ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ምክንያት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በሀገራችን በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ባለሀብቶች አፍ ጠፍቶ የማያውቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዛሬ ላይ ታሪክ ሆኗል።

ለዐሥርት ዓመታት የዘለቀው ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዋናነት የመነጨው የሀገራችን የወጪ ንግድ ገቢ 3 እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ባልበለጠበት ሁኔታ የገቢ ንግድ ፍላጎት 14 እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር በመድረሱ ከተፈጠረው ከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ለመሠረተ ልማት የተወሰዱ የውጭ ብድሮች የክፍያ ጫና እና የብር ዋጋ በሰው ሠራሽ መንገድ ታግቶ በመያዙ በመደበኛው እና በጥቁር ገበያው መካከል 100% እና ከዚያ በላይ የዋጋ ልዩነት ፈጥሮ ነበር።

ይህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአቅማቸው በታች እንዲያመርቱ፣ የነዳጅ እና መድኃኒት አቅርቦት እንዲስተጓጎል እና የዋጋ ንረት እንዲባባስ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ይህንን ችግር ለመቀየር ብሔራዊ ባንኩ በሐምሌ 2016 . ታሪካዊ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የምንዛሪ ተመን በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን አድርጓል።

ከዚሁ ጎን ለጎን 13 ራሳቸውን የቻሉ ነጻ የምንዛሪ ቢሮዎች (Independent Forex Bureaus) እንዲቋቋሙ በመፍቀድ፣ የላኪዎችን የውጭ ምንዛሪ ማቆየት መብት በማሻሻል እና ለንግድ ባንኮች በጨረታ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ሰፊ ዕርምጃዎችን ወስዷል።

የእነዚህ ዕርምጃዎች ውጤት በቁጥር ሲመዘን፣ በመደበኛው ባንክ እና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው 100% በላይ የዋጋ ልዩነት ወደ 5 እስከ 10 በመቶ ዝቅ ብሏል። እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ብሔራዊ ባንክ ከሚወስነው ቋሚ ተመን ወጥቶ በገበያ እንዲመራ መደረጉ፣ የኢትዮጵያን የወጪ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተወዳዳሪ አድርጎታል።

በናትናኤል ጸጋዬ

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: