የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረጋቸው የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያዎች የሀገራችንን የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ምኅዳር ከመሠረቱ ቀይረውታል።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁለት የመንግሥት ባንኮች፣ 30 የግል ባንኮች፣ 19 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 63 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን፣ 13 የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች፣ 17 የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት አቅራቢዎችን እና 5 የካፒታል ዕቃዎች የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶችን ያስተዳድራል።
ታዲያ እነዚህን በድምሩ 149 የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የሚያስተዳድረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ማዕከላዊ ባንክነቱ የዋጋ ማረጋጋትን፣ የፋይናንስ ተቋማትን ደኅንነት እና ጤናማነት ለማረጋገጥ ይሠራል።
የባንኩ ምክትል ገዢ እና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ እንደሚያረጋግጡት፣ ከሪፎርሙ በፊት በርካታ ግቦችን እኩል ለማሳካት ይደረግ የነበረው ጥረት ተሻሽሎ፣ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት የባንኩ ቀዳሚ ትኩረት ሆኗል።
በዚህ የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃ፣ 30 በመቶ ደርሶ የነበረው የዋጋ ንረት በፈረንጆቹ 2025 ወደ ነጠላ አኀዝ ወርዶ የነበረ ሲሆን፣ በሰኔ 2026 ደግሞ ከ13.9 በመቶ እንዳያልፍ ማድረግ ተችሏል።
ከታሪካዊ ስኬቱ ጀርባ፣ ገለልተኛ ምሁራንን ያካተተ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በሕግ መቋቋሙ እና ጥልቅ ትንተና ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መሰጠቱ ትልቅ ድርሻ አለው።
መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በሚወስደው ብድር ላይ ጥብቅ ሕጋዊ ገደብ በመጣሉ፣ ብድሩ በፖሊሲ ወለድ ታስቦ በ12 ወራት ውስጥ መመለስ እንዳለበት በሕግ የተደነገገ ሲሆን፣ መንግሥትም ላለፉት ዓታት ምንም ዓይነት ብድር ባለመውሰድ ለሪፎርሙ ያለውን አስደናቂ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።
ማሻሻያው በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እና አስተዳደር ላይ ጉልህ መነቃቃትን ፈጥሯል። ቀደም ሲል ከ3.5 ቢሊየን ዶላር ያልዘለለው የወጪ ንግድ ገቢ ወደ 11.2 ቢሊዮን ዶላር በማደግ፣ በሦስት ዓመታት ሪፎርም ብቻ 24 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።
ከአንድ ወር በታች የገቢ ንግድን ይሸፍን የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት (Reserve) ደግሞ የ4 ወራት ሽፋን ወደመስጠት አድጓል።
በናትናኤል ጸጋዬ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: