ኢትዮጵያ የታሪኳን አቅጣጫ የሚቀይር ታላቅ የልማት እና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።
የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ በተበታተኑ ጥረቶች ሳይሆን፣ ዐበይት የልማት አእማድን እርስ በእርስ በማስተሳሰር እና የመደመር አስተሳሰብን መሠረት በማድረግ የሚመራ ነው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እና የቱሪዝም ዘርፍ ተነጣጥለው የሚታዩ ተግባራት አይደሉም፤ ይልቁንም አንዱ ለሌላው ተጨማሪ አቅም እየሆነ ሀገራዊ ማንሰራራትን የሚያፋጥኑ የተጣመሩ የልማት ሞተሮች ናቸው።
መደመር ማለት አቅሞችን ማጣመር፣ የተበታተኑ ሀብቶችን ማስተሳሰር እና ከክፍሎች ድምር በላይ የሆነ ታላቅ ውጤት ማስመዝገብ ነው።
የአፍሪካ ግዙፉ እና የሀገራችን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተሳፋሪዎችን እና የንግድ ማኅበረሰብን ወደ ሀገር ውስጥ ሲያጓጉዝ፣ በከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት ደግሞ ምቹ፣ ጸዱ እና ሳቢ የዲፕሎማሲና የንግድ ማዕከልን ያቀርባል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ"ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" መርሃ ግብሮች የተገነቡት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ እና ጨበራ ጩርጩራ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መስህቦችን በከፍተኛ ደረጃ አስፍተዋል።
ይህ የተቀናጀ ትስስር የቱሪዝም ዘርፉን አበልጽጎ የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው ይገኛል።
የመንገድ፣ የባቡር፣ የኃይል እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶች መስፋፋት የኢትዮጵያን የልማት መስመሮች አስተሳስረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ታዳሽና ንፁህ ኃይል ኢንዱስትሪዎችን ከመመገቡም በላይ፣ የቴሌኮም እና የዲጂታል አሠራር ዝርጋታን ያፋጥናል።
አዲሶቹ የመንገድ እና የአየር መንገድ መስመሮች ደግሞ ምርት እና አገልግሎት በፍጥነት ወደ ገበያ እንዲደርስ በማድረግ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ክፍሎችን ያገናኛሉ።
ይህም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻሉም በላይ የተለያዩ አካባቢዎችን የኢኮኖሚ ውህደት እውን አድርጓል።
የእነዚህ የተቀናጁ ፕሮጀክቶች ትልቁ ስኬት ግንባታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ፕሮጀክቶቹን በተቀመጠላቸው አጭር ጊዜና በጥራት ማጠናቀቅ የተቻለበት የመንግሥት የላቀ የመፈጸም አቅም ጭምር ነው።
ቀደም ሲል የነበረውን ፕሮጀክቶች የመጎተትና በወረቀት ላይ የማስቀረት ልማድ በመቀየር፣ በ24/7 የሥራ ባህል ፈጣን ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
ይህ አዲስ አሠራር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመደመር ዕሳቤ የተቃኘና የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ በሕዝቡ ዘንድ "ሠርቶ መለወጥ ይቻላል" የሚል ታላቅ ሀገራዊ በራስ መተማመንን ፈጥሯል።
በመደመር እይታ የተገነባው የልማት ቅንጅት የዛሬን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ለነገው ትውልድ የሚሻገር ፅኑ መሠረት ጥሏል።
የኮሪደር ልማትና የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አረንጓዴና ዘላቂ ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ የተገነቡ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የተግባር ምላሾች ናቸው።
እነዚህ ሥራዎች በአንድ በኩል ለሺዎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ሲፈጥሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታና ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።
በተቀናጀ አቅም እና በተግባራዊ የመፈጸም ባህል የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: