ኢትዮጵያ ከግብርና መራሽ ኢኮኖሚ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር የአምራች ዘርፍ እድገት ወሳኝ ድርሻ አለው።
በዚህ ታሪካዊ የማንሠራራት ዘመን እና የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚው ዋና ምሰሶ በመሆን በመስራት ላይ ይገኛል።
በተለይም ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሬ በማመንጨት፣ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት እና አስተማማኝ የዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ኮርፖሬሽኑ እያከናወነ ያለው ተግባር ስትራቴጂካዊ ፋይዳው የጎላ ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት ኤክስፖርት ተኮር የሆኑ አምራች ኩባንያዎችን ለመሳብ ታስበው የተደራጁ ቢሆንም፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን አጠቃላይ ሚና ከፍ ለማድረግ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች (SEZs) እንዲሸጋገሩ አስፈላጊው ሕጋዊ እና መዋቅራዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ኮርፖሬሽኑ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባሻገር የሚስባቸው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) ዓይነቶች ዘርፈ ብዙ እንዲሆኑ አድርጓል።
በዚህም ቀደም ሲል ይተኮርባቸው ከነበሩት እንደ አልባሳት፣ ጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ ውጤቶች እና የግብርና ማቀነባበሪያ ባሻገር የከፍተኛ ቴክኖሎጂ እና የመድኃኒት ማምረቻ ዘርፎችን እንዲያካትቱ ተደርጓል።
ይህ የሽግግር ሂደት የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ምርቶች ዓይነት እና መጠን ከማሳደጉ ባሻገር፣ በየዓመቱ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ እና የዜጎችን የክህሎት እድገት በማስፋት ረገድ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ነው።
በፓርኮቹ እና በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ ውስጥ የሚሠሩ አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ ገበያዎች በስፋት ከማቅረብ ባሻገር፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ስትራቴጂካዊ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በማድረግ ረገድ የራሳቸውን ታላቅ ዐሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ።
ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥ እና የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለማቃለል የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ አምራቾች እና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ላለው የገበያ ዕድል ጠንካራ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
አርሶ አደሮች፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን አምራቾች ለትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ እንደ ጥጥ፣ ቆዳ እና የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በግብአትነት እንዲያቀርቡ ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ተደርጓል።
ይህ አሠራር የሀገር ውስጥ እሴት ሰንሰለትን ያጠናከረ ሲሆን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድም አዲስ የመነቃቃት መንፈስ ፈጥሯል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚተዳደሩት ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ዓለም አቀፍ ጥራታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው፣ በዓለም ላይ ታዋቂ ከሆኑ ብራንዶች እና የኢንዱስትሪ ምርት አከፋፋዮች ጋር በቀጥታ ማስተሳሰር ተችሏል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ተወዳዳሪ እና ተራጭ እንድትሆን ሰፊ በር ከፍቷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በማስተሳሰር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት፣ ለአስር ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ አቅምን በማጎልበት ረገድ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ነው።
ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ይህንን የማንሠራራት ዘመን ጅምር ይበልጥ ማጠናከር፣ የአሠራር ማነቆዎችን መፍታት እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ ነው።
የኮርፖሬሽኑ ስኬት የነጠላ ተቋም ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጫ ቁልፍ ምሰሶ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: