የ2018 ዓመተ ምሕረት የልማት ጉዞ በኢትዮጵያ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ጅማሮ፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፍሬዎች እና በላቀ የማክሮ ኢኮኖሚ ስኬት የተለየ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህ ዓመት የተጀመሩት እና ፍጻሜ ያገኙት ተግባራት የግንባታ ስኬቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሀገራችንን የማምረት አቅም ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና ዘላቂ የኢኮኖሚ መሠረት ለመጣል የታለሙ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው።
በሶማሌ ክልል የሚገኘው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ካሏት የተፈጥሮ ሀብቶች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እሴት የምታደርገውን ሽግግር የሚያሳይ ቀዳሚ ማረጋገጫ ነው።
ሀብትን ከመሬት ስር አቅቦ ከማቆየት ይልቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እሴት በመጨመር ለሀገር ኢኮኖሚ ማዋል የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ነው።
ይህ የጋዝ ልማት የኢነርጂ አቅርቦትን ከማስፋት ባሻገር፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የኃይል መሠረት በመሆን እና ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ስትራቴጂካዊ ሀብት ነው። የተፈጥሮ ጋዙ ግንባታው ለተጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግብአት በመሆን ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምግብ ሉዓላዊነት ጉዞን ተጨባጭ የሚያደርግ ነው፡፡
በአቪዬሽን ዘርፍ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስገነባው የቢሾፍቱ (አቡሰራ) ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትስስር አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።
በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይዞ የሚገነባው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የተጓዦች ማረፊያ ብቻ ሳይሆን የንግድ፣ የቱሪዝም፣ የውጭ ንግድ እና የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴዎችን የሚያፋጥን አህጉራዊ የኢኮኖሚ ሞተር ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአቪዬሽን ዘርፉን አቅም በማላቅ በሆቴል፣ በቱሪዝም እና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ለአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የሚገነባው የዘመናዊ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልማትን በቀጥታ የሚያገናኝ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና መደገፊያ እንደመሆኑ መጠን፣ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ጥገኝነት ከመቀነሱም በላይ በየዓመቱ ለግዥ ይወጣ የነበረውን አያሌ የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል።
ይህም ለአርሶ አደሮች የግብዓት ተደራሽነትን በማረጋገጥ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር እና የምርት ብክነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በግንባታቸው ወቅትም ሆነ ወደ ሙሉ አገልግሎት ሲገቡ ከመሐንዲሶች እስከ ቴክኒሻኖች፣ ከሎጂስቲክስ እስከ አገልግሎት ሰጪዎች ድረስ ለብዙ ሺህ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው።
ከዚህ ጎን ለጎን የተመዘገበው የሀገር ውስጥ ገቢ ሰብሳቢነት እድገት እና የኤክስፖርት ገቢ መሻሻል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የተቀናጀ የልማት ጉዞ በተጨባጭ የሚያረጋግጡ ናቸው።
ተፈጥሯዊ ሀብትን ወደ ኢኮኖሚ እሴት መቀየር፣ የመጓጓዣ እና የሎጂስቲክስ ትስስርን ማዘመን፣ የኢነርጂ አቅርቦትን ማበራከት እና ግብርናን በኢንዱስትሪ ማገዝ የኢትዮጵያን ነገ የሚወስኑ የዕድገት ማዕዘናት ናቸው።
ዛሬ የሚጣሉት መሠረቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: