Search

በአፍሪካ በግዙፍነቱ 5ኛ ደረጃን የያዘው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በዛምቢያ

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 243

በታዳሽ ኃይል ልማት ትልቅ እርምጃ እየወሰደች ያለችው ዛምቢያ 100 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በይፋ ጀምራለች። 

ቺሳምባየሚል ስያሜ የተሰጠው የፀሐይ ኃይል ማመንጫው በሀገሪቱ 90 ሺህ ገደማ አባዎራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል። 

ፕሮጀክቱ በግብፅ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ቀጥሎ በግዙፍነቱ ከአፍሪካ 5 ደረጃን እንደሚይዝ ነው የተነገረለት።

ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ይህም በቀጣናው ያሉ ሀገራት በታዳሽ ኃይል ላይ እያደረጉ ያለው ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱን ያመላክታል። 

ዛምቢያ ለፕሮጀክቱ ግንባታ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ተገልጿል፤ ይህም የፕሮጀክቱን ግዙፍነት እንዲሁም ሀገሪቱ የኢነርጂ አቅሟን ለማስፋት ያላትን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃል።

ቺሳምባየፀሐይ ኃይል ማመንጫ ሀገሪቱን ከባህላዊ የኃይል አቅርቦት ጥገኝነት እንደሚያላቅቅ፣ ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታገኝ እንደሚያደርግ እንዲሁም ለቢዝነሶች መነቃቃትን በመፍጠር የኢኮኖሚ ዕድገቷን እንደሚደግፍ ታምኗል።

ከዚህም ባሻገር በዓመት እስከ 150 ሺህ ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀትን በመቀነስ ዛምቢያ የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚያበርክትም ይጠበቃል ሲል የዘገበው ማላዊ24 ነው።
በዮናስ በድሉ