Search

ኦሮሚያ ባንክ "አባ ፈርዳ" የተሰኘ አዲስ የዲጂታል ሐዋላ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

ማክሰኞ ጳጉሜን 03, 2018 88

ኦሮሚያ ባንክ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ የሚልኩበትን "አባ ፈርዳ" የተሰኘ ዘመናዊ የዲጂታል ሐዋላ መተግበሪያ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ከካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ . ጋር በመተባበር ያቀረበው ይህ አዲስ የዲጂታል ሐዋላ አማራጭ፣ ደንበኞች የቦታ እና የጊዜ ገደብ ሳይኖርባቸው ከመላው ዓለም በሞባይል መተግበሪያው አማካኝነት በቀላሉና በፍጥነት ገንዘብ እንዲልኩ ያስችላቸዋል።

በዚህ ቴክኖሎጂ የሚላከው ገንዘብ በቀጥታ ወደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ባንክ ሒሳብ፣ የሞባይል ዋሌት እና የነጋዴዎች የክፍያ አማራጮች የሚደርስ በመሆኑ ተቀባዮች በለመዱት የፋይናንስ ሥርዓት ገንዘባቸውን መቀበል ይችላሉ።

ተጠቃሚዎች ከውጭ ሀገር ሆነው እንደ ትምህርት ቤት ክፍያ፣ የሕክምና ወጪ ወይም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች በቀጥታ ለሚመለከተው ተቋም ክፍያ መፈጸም የሚያስችላቸው አማራጭ ተካቷል።

በከፍተኛ የኢንክሪፕሽን ቴክኖሎጂ የተጠበቀው መተግበሪያው፣ የዲጂታል ግብይቱን አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ ያደርገዋል።

ይህ አዲስ አገልግሎት የሐዋላ መስመሩን በማዘመን የዳያስፖራውን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሕጋዊው የባንክ ሥርዓት ለማስገባት እና ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ከዚህም ባሻገር መተግበሪያው ባካተተው የበጎ አድራጎት ማዕቀፍ፣ ዳያስፖራው ለአገራዊና ማኅበረሰባዊ ፕሮጀክቶች በቀላሉ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የፋይናንስ አካታችነት እና የኢኮኖሚ ከፍታ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሀገራዊ ስኬት ነው።

 

በሳምሶን በላይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: