የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት ከዋዜማው ዕለት ጀምሮ የሚያጋጥሙ የኃይል ችግሮችን ለመፍታት 24 ሰዓት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የቴክኒክ ቡድን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
ተቋሙ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስና ድንገተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን የጥገና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አጠናቅቆ ወደ ተግባር ገብቷል።
በዚሁ መሠረት በበዓሉ ወቅት የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ በመላ ኢትዮጵያ 2 ሺህ 110 ኪሎ ሜትር የኃይል መስመር እና ከ8 ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
በተጨማሪም በዋዜማው ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የኃይል ጭነት ለመቋቋም የሚያስችል የ178 ትራንስፎርመሮች አቅም ማሻሻያ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 88ቱ በአዲስ አበባ እና 90ዎቹ ደግሞ በክልል ከተሞች የሚገኙ ናቸው።
ተቋሙ በበዓሉ ወቅት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማመጣጣን ደንበኞች ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ እና በተለይም የኃይል ጭነት በማይበዛበት ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባለው ጊዜ ኤሌክትሪክ በመጠቀም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
ህብረተሰቡ ድንገተኛ የኤሌክትሪክ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ወይም የጥገና ጥቆማ ለመስጠት በነፃ የስልክ መስመር 905 በመደወል ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: