Search

ኢትዮጵያ፦ በአንድ ውብ ሸራ ላይ የተሣለች ሕያው የሕብረ ቀለማት ሥዕል

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 49

ኢትዮጵያ ከተንጣለለው የራስ ዳሸን ተራራ ጫፍ እስከ ዝቅተኛው የዳሎል ስምጥ ሸለቆ፣ ከምሥራቁ የሐረር ግንብ እስከ ምዕራቡ የጋምቤላ ለምለም ጫካዎች ድረስ ስትቃኝ፣ በአንድ ውብ ሸራ ላይ የተሣለች ሕያው የሕብረ ቀለማት ሥዕል ናት።

ይህች ምድር የብዙ ሺህ ዘመናት የትውልድ ሐረግ የተሣሠረባት፣ የባህል፣ የቋንቋ እና የእምነት ብዝኃነት ደምቆ የሚታይባት ታላቅ ሀገር ናት። የዚህች ሀገር እውነተኛ ውበት እና የአይበገሬነት ምሥጢር የሚገኘው ደግሞ ከተለያዩ ባሕሎች እና ማንነቶች በተፈተለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ውስጥ ነው።

የኢትዮጵያውያን የወል ትርክት የተገነባው እኔ ከሚለው ይልቅ እኛ በሚለው ጽኑ ማኅበራዊ መሠረት ላይ ነው። በኢትዮጵያ መንደሮች ውስጥ ብዝኃነት የመለያያ ሰበብ ሳይሆን፣ መረዳዳት እና መተሳሰብ የሚጎላበት የውበት መገለጫ ነው።

ከጥንት ጀምሮ አባቶቻችን እና እናቶቻችን በደቦ አብረው አርሰዋል፤ በዕድር ተደጋግፈዋል፤ በዕቁብ አብረው ሕይወትን ለመለወጥ ለፍተዋል። እነዚህ ሀገር በቀል እና ባህላዊ የመረዳዳት ዕሴቶቻችን፣ የሰው ልጅን ክብር ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድሙ፣ በባሕርያቸው ደሃ ተኮር እና ጥልቅ የሆነ ሰብዓዊነትን ያዘሉ የኅብረት መገለጫዎች ናቸው።

በጎረቤት ቤት እሳት ሲጠፋ ከራስ ምድጃ ትኩስ ረመጥ ማካፈል፣ በችግር ጊዜ ጉልበትን አስተባብሮ ደካማውን መደገፍ የዘመናት የኢትዮጵያውያን መለያ ነው።

እነዚህ ጥልቅ የሆኑ ባህላዊ የመረዳዳት ዕሴቶች ዛሬ ላይ ለተጀመረው ዘመናዊ ሀገራዊ መግባባት እና ደሃ ተኮር ለሆኑ የልማት ሥራዎች ጽኑ መሠረት ናቸው።

የመደመር መንግሥት ይህንኑ የሕዝቦቿን ጥንታዊ የሰብዓዊነት እና የመተሳሰብ ዕሴትን የዘመናዊ ልማት ፍልስፍናው ማዕከል አድርጎ እየሠራ ይገኛል።

ልማት ማለት የሕንፃ ከፍታ ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅን ክብር ከፍ ማድረግ እና ከድህነት ማውጣት ነው በሚል መርሕ፣ ሰብዓዊነትን የሀገር ግንባታ እና የፖሊሲ ማዕከል ማድረግ ደግሞ ባሕላዊ የወል ትርክታችን ዘመናዊ ትርጉም የሚሆን ነው።

አዲሱ የልማት አቅጣጫ ብዝኃነትን ማስተናገድ መቻል ለሀገር ልማት ያለውን ወሳኝ ሚና በተግባር ያረጋገጠበት፣ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚመነጩ ዕምቅ አቅሞችን ለጋራ ብልጽግና አቀናጅቶ ለመጠቀም ያስቻለ ነው።

ይህ ሰብዓዊነትን እና ኅብረብሔራዊ አንድነትን ያነገበው ራዕይ፣ ሀገራዊ ምክክርን በስኬት በማካሄድ በኩል ትልቅ ፍሬ አፍርቷል።

በስኬት የተጠናቀቀው የሀገራዊ ምክክር ሒደትም ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በሽምግልና፣ የዛፍ ጥላ ሥር እና በየባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶቻቸው ሲያደርጉት የነበረውን ቁጭ ብሎ የመነጋገር ልማድ ወደ ብሔራዊ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው።

በምክክሩ መድረክ የተለያየ ሐሳብ፣ የተለያየ ቋንቋ እና የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች በአንድነት በመወያየት ልዩነቶቻቸው የጋራ ጠላታቸው አለመሆኑን በተግባር አሳይተዋል። ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ የሆነች ሀገር ለመገንባት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት አሳይተዋል። ይህ ባህላዊ ዕሴቶቻችን ለዘመናዊ የፖለቲካ መግባባት እንዴት ድልድይ እንደሆኑ በግልጽ ይመሰክራል።

የኢትዮጵያ ጥንካሬ ያለው በኅብረቷ ውስጥ ነው! ልክ እንደ ሸማ ክር፣ አንዱ ቀለም ከሌላው ጋር ተሰናስሎ ያንን ውብ እና ደማቅ ጥለት እንደሚፈጥር ሁሉ የኢትዮጵያ ልጆችም ተደምረው ባለ ደማቅ ሕብረ ቀለሟን እና በኅብረቷ የጠነከረችውን ሀገር በአንድነት ያጸናሉ።

ሰብዓዊነትንም የልማታቸው ማዕከል በማድረግ እና በሀገራዊ ምክክር የጋራ መግባባትን በመፍጠር፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምታኮራ እና የበለጸገች ሀገርን ለማቆየት ጉዟቸውን አጠናክረዋል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: