ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2019 አዲሱ ዓመት ባስተላለፉት የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ለትውልድ የሚተርፍ አስደናቂ ታሪኮችን እየሰራን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በአረንጓዴ ዐሻራ፤ ቱሪዝምን በገበታ ፕሮጀክቶች፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በበጋ ስንዴና በሌማት ትሩፋት፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በኢትዮጵያ ታምርት እየገነባንና እያጸናን ነው።
የኢነርጂ ዐቅማችንን በተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትና ኑክሌር ቴክኖሎጂ ለማሳደግ፣ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን፣ የአየር መንገድ አድማሳችንን በግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ለማስፋት ነገን አስበን ዛሬ እየተጋን ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
የሕዳሴ ግድብን ፍጻሜ፣ የመስኖ ግድቦችን ፍሬ፣ የሩዝ ምርትን ከፍታ፣ የፍራፍሬ ምርትን ተአምር፣ የወጪ ንግድን ጭማሬ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያችንን ውጤት፣ በአፍሪካ የፈጠርነውን የኢነርጂ ትሥሥር፣ ዲጂታል 2030ን ስኬት፣ የኮሪደር ልማታችን የኢትዮጵያን ሀብትና ውበት መግለጥ የዘመን መጽሐፋችን እየመዘገበ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማታችን አፈራችንንም፣ ከተማችንንም፣ ጤናችንንም፣ ውኃችንንም እየጠበቀ መሆኑን፣ መድኃኒት የማምረት ደረጃና ዐቅማችም እያደገ መሄዱን፣ የማዕድን ፍለጋችን፣ ምርታችንና ሽያጫችን የዘመናት ስብራትን እየጠገነ መምጣቱንም አስረድተዋል።
የባሕር በር አጀንዳችን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ማግኘቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ የተጽዕኖ አድማስ መስፋቱን አመላክተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: