ከትናንት ወዲያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በዳኝነት ባገለገሉበት በርካታ አመታት የተለያዩ ጉዳዮችን ከህግና ከሰብዓዊነት አንጻር በሚበይኗቸው ፍርዶች በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ መግባት የቻሉ ነበሩ።
ዳኛ ካፕሪዮ በነዚህ ዘመናት ብዙዎችን ያስገረመ ፍርድ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የትራፊክ ሕግ በመተላለፍ በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ የነበረው የኢትዮጵያዊው ሀሰን አብዲ ታሪክ በወቅቱ መነጋገሪያ ነበር።
ሀሰን አብዲ በእለቱ ፍርድ ቤት የተገኘው ባልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬትና በሌሊት መኪና ማቆም በተከለከለበት ቦታ መኪናውን በማቆሙ ነው።
ዳኛ ካፕሪዮ የተለያዩ የቅጣት ወረቀቶች እንደቀረበበት ከተናገሩ በኋላ ሁሉም ጥፋቶች የተፈፀሙት በሪሰርቫየር ጎዳና አካባቢ ነው መኖሪያህ እዛ ነው ሲሉ ጠየቁት።
“አዎ” ሲል መለሰ፤ እና ለሊቱን ሙሉ እዛ ነው ያቆምከው ልክ ነኝ። ትክክል ነዎት ክቡር ዳኛ ሲል መለሰ፤ መኪናውን በዛ ስፍራ ላይ ያቆመው ልጄ ነበር።፡
ልጅህ የት ነው የሚማረው? ሲሉ ጠየቁት ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው ክቡር ዳኛ፤ እና እሱ መገኘት ያልቻለው ትምህርት ስለሄደ ነው?
“አዎ ዳኛ” ካፕሪዮ ሀሰንን እየተመለከቱ በመቀጠል ስንት ልጆች አሉህ ሲሉ ጠየቁት። “ሁለት” ሲል መለሰ። ሁለቱም ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው የሚማሩት?
ምንድነው ልጅህ የሚያጠናው? ትምህርቱን ሲጨርስስ ምን ለመሆን ያስባል ሀኪም ነው ወይም ዳኛ?
ሀሰን ሁለቱም ልጆቹ ፕሮቪደንስ ኮሌጅ እንደሚማሩ አንደኛው ልጁ ጠበቃ መሆን ነው እንደሚፈልግ ነገራቸው ።
ዳኛ ካፕሪዮ ልጁ ጠበቃ መሆን የሚፈልግ ከሆነ ዛሬ በችሎት ቢገኝ ጥሩ ልምድ ይቀስም እንደነበር ከተናገሩ በኋላ በድንገት ከየት ሀገር እንደመጣና ምን ያህል ጊዜ እንደሆነው ልጁ የተወለደው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነ አከታትለው ጠየቁት። ሀሰን አብዲ ወደ አሜሪካ ከመጣ 16 አመታት እንዳሳለፈ። ልጁ በኬንያ ስደት ላይ በነበረበት ጊዜ መወለዱን ነገራቸው።
ዳኛ ካፕሪዮ ወደ አቃቤ ህጉ እየተመለከቱ ሀሰን ከዚህ በፊት በህግ መተላለፍ ሪከርድ እንደሌለበት እና ለእሱና ለልጆቹ የተሻለ ህይወት ለመፍጠር እየተጋ እንደሆነ መረዳታቸውን ገልፀውለት ወደ ፍርድ ከመሄዳቸው በፊት ሁሌ እንደሚያደርጉት የሀሰንን የኋላ ታሪክ ለማወቅ ምን እንደሚሰራ፣ ለምን ያህል ጊዜ በስራ እንደሚያሳልፍ ይጠይቁት ጀመር።
ሀሰን ከጥቂት ጊዜያት በፊት መደብር ከፍቶ እንደነበር ሆኖም አሁን እንደሸጠው በቀን ውስጥ ለ16 ሰዓታት እንደሚሰራ ለዳኛ ካፕሪዮ ተናገረ።
ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ይህን እንደሰሙ ሀሰንን በአድናቆት እየተመለከቱ ከኢትዮጵያ መጥቶ ለ16 ሰዓታት እየሰራ ሁለቱንም ልጆቹን ኮሌጅ ማስተማር መቻሉን አድንቀው፤ ለሌሎችም ወላጆች አርአያ መሆን በሚችል መልኩ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በአድናቆት ከተናገሩ በኋላ የእሳቸውን የልጅነት ታሪክ በማስታወስ ስለ አባታቸው መናገር ጀመሩ።
ታውቃለህ ልጅ እያለሁ ትዝ ይለኛል አባቴ ከሌሊቱ አስር ሰአት እየተነሳ ነበር ወደስራ የሚሄደው። እና እሱ ባለፈበት አስቸጋሪ የህይወት መንገድ እንዳልሄድ በርትቼ መማርና ኮሌጅ መግባት እንዳለብኝ ይመክረኝ ነበር።
እና ያንተም ልጆች አንተን እያዩ ይህንን ይገነዘባሉ ለልጆችህ ጥሩ ትምህርት እየሰጠህ ነው በማለት የሀሰንን የስራ ትጋት አድንቀው ወደ ፍርድ አሰጣጡ ሂደት መግባት ጀመሩ።
እንግዲህ እዚህ ላይ መኪናውን የተከለከለ ቦታ ለቆመበት ላልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬት ከቆመበት ቦታ የተጓጓዘበትን ጨምሮ በድምሩ የ300 ዶላር ቅጣት ተፅፎብሃል ሆኖም ተምሳሌት መሆን የምትችል መልካም አባት በመሆንህ 160 ዶላር ብቻ እንድትከፍል ወስኛለሁ እና ይህን መክፈል ትችላለህ ሲሉ ጠየቁት።
ሀሰን በመልካሙ ዳኛ ፍርድ ተስማምቶ “አዎ መክፈል እችላለሁ” ሲል መለሰ።
ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ሀሰን የተወሰነበትን ቅጣት መክፈል እንደሚችል ከሰሙ በኋላ በትጋቱ እና በመልካም ተምሳሌትነቱ ያደነቁትን ኢትዮጵያዊውን አባት በዚሁ መልካም ተግባሩ እንዲቀጥል መክረውትና መልካም ህይወት እንዲያጋጥነው ተመኝተውለት ሸኝተውታል።
እኚህ ምስጉን ዳኛ ለ40 ዓመታት በዳኝነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ባለፈው አመት ጡረታ መውጣታቸው ይታወሳል ።
በዋሲሁን ተስፋዬ