Search

ኢሬቻ፦ የብዝኃነት እና የሕዝቦች አብሮነት መገለጫ

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 84

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከተፈጥሮ፣ ከፈጣሪው እና ከወገኑ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት የሚያሳይበት የምስጋና ሥርዓት ነው። በዓሉ ከባህላዊ ክዋኔነቱ ባሻገር የላቀ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ትርጉም ያዘለ ታላቅ በዓል ነው።

ይህ ሥርዓት በፍጡራን እና በፈጣሪ (ዋቃ) መካከል ያለውን ሕልውናዊ ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችለውን "ሰፉ" የተሰኘውን የሥነ-ምግባር እሴት በተግባር የሚያሳይ ነው።

ከክረምት ጨለማ ወደ ብሩሁ የጸደይ ወቅት የሚደረገውን ሽግግር ተከትሎ የሚከበረው የኢሬቻ መልካ ሥርዓት በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ መንፈሳዊ እርካታን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የሕዝቦችን ማኅበራዊ ትሥሥር እና የብዝኃ-ባህል አብሮነትን በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል።

ኢሬቻ የማኅበራዊ ካፒታል ግንባታ እና የሰላም ድልድይ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የተራራቁ ወገኖች በበዓሉ ላይ በመሰባሰብ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን ያጠናክራሉ።

በሥርዓቱ ውስጥ የሲንቄ ባለቤት የሆኑት እናቶች (ሃደ ሲንቄዎች) በምርቃት እና በጸሎት የሚያበረክቱት ግንባር ቀደም ተሳትፎ፣ የሴቶችን የተከበረ ማኅበራዊ ስፍራ እና የፆታ እኩልነትን በጉልህ ያሳያል።

የሲንቄ ዘንግ የሰላም እና የፍትሕ ተምሳሌት እንደመሆኑ፣ የሴቶች እና የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ወጣቶች ባህላዊ እሴቶችን እንዲወርሱ እና የማኅበረሰብ አደራን በኃላፊነት እንዲረከቡ ያዘጋጃል።

የኢሬቻ እሴት ለአንድ የተወሰነ ወገን ብቻ የተከለለ ሳይሆን፣ ማንኛውንም የሰው ልጅ በእኩልነት የሚያስተናግድ ጥልቅ የብዝኃ-ባህል መድረክ ነው።

ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በበዓሉ ቦታ በመገኘት ባህላዊ አልባሳታቸውን እና ውበታቸውን ያንጸባርቃሉ።

ይህ ዓይነቱ ወሰን ተሻጋሪ መስተጋብር በሕዝቦች መካከል የጋራ መከባበርን እና ወንድማማችነትን ያጎለብታል።

ይህንን ብሩህ አብሮነት የሚያንጸባርቅ እሴት ጠብቆ ማቆየት እና ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር፣ ዘላቂ ሰላምን እና የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ ነው።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: