ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 11.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ ገለጹ።
ከዚህ ውስጥ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዘርፍ ድርሻ የ572.9 ሚሊዮን ወይም የ5 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት "የማይበገር ንግድ እና ዘላቂ የእሴት ሰንሰለት" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች በተፈጥሯዊ ይዘታቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳላቸው የጠቆሙት ወይዘሮ ያስሚን፣ የዘርፉ የወጪ ንግድ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት ማሳየቱን እና ያልተነካ ሰፊ አቅም መኖሩን አመላክተዋል።
መንግሥት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምኅዳሩን ይበልጥ ተወዳዳሪ እና ምቹ ለማድረግ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረታዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አስረድተዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በዘመናዊ እርሻ፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ በምግብ ዘይት ማምረቻ፣ በማከማቻ መጋዘኖች እንዲሁም በምርት ማበጠርና ማሸግ ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በይፋ የጀመረችው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የዕቃዎች ንግድ ትግበራ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያለውን አህጉራዊ ገበያ በመክፈት ለዘርፉ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ፣ ሂደቱ የንግድ ሥርዓቱን ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር በማስተሳሰር ለንግድ አጋሮች አስተማማኝና ግልጽ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር አረጋግጠዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: