ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት፣ ከሰማንያ በመቶ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ የሕልውና መሠረትና የወጪ ንግድ ዋነኛ ምንጭ ነው።
ሆኖም ለአሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነት ወሳኝ በሆነው የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ሙሉ በሙሉ በውጭ አቅርቦት ላይ ተመሥርቶ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ከውጭ ስታስገባ፣ እንደ ዓለም ገበያ ሁኔታ በመቶ ሚሊዮኖች እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች።
ይህ ከፍተኛ ወጪ ለመሠረተ ልማት፣ ለመድኃኒትና ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች የሚውለውን ውስን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በእጅጉ ሲሻማ ቆይቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ሲንርና የአቅርቦት ሰንሰለቶች ሲስተጓጎሉ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ቢያደርግም፣ የዋጋ ጭማሪው በአርሶ አደሩ የምርት ወጪ ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል።
ከዚህም ባለፈ ማዳበሪያ በመርከብ ተጓጉዞ በወደብ በኩል አልፎ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ እስኪደርስ የሚፈጠር ትንሽ መዘግየት የዝናብ ወቅትን በማሳለፍ በሰብል ምርታማነት ላይ የማይተካ ጉዳት ያደርሳል።
ይህንን መሠረታዊ ችግር ከስሩ ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር በነሐሴ 2017 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጎዴ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በይፋ አስጀምራለች።
በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባውና በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው ይህ ግዙፍ ፋብሪካ፣ በዓለም ካሉ ትላልቅ የማዳበሪያ አምራች ተቋማት አንዱ ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የዩሪያ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን አልፎ ለቀጣናው ገበያ የመላክ አቅም ይፈጥራል።
የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ የሚያስገኘው ፋይዳ በግብርናው ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። እነዚህ ግዙፍ የኬሚካልና የኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች፣ ቴክኒሻኖችና ሠራተኞች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
የኬሚካል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሸጋገር በማድረግም ለሌሎች ተዛማጅ ኢንዱስትሪዎች የእሴት ሰንሰለት ግንባታ ትልቅ ጉልበት ይሆናሉ።
ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ምርት የሚያስፈልጉ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ናት። በሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ የሚገኘው ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለዩሪያ ማዳበሪያ ምርት ዋነኛው ጥሬ ዕቃ ሲሆን፣ በአፋር ክልል ዳሎል የሚገኘው ሰፊ የፖታሽ ክምችትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፎስፌት ሀብቶች ደግሞ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድ ግዙፍ የማዳበሪያ አምራችና አቅራቢ ያደርጓታል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ እየለማ ያለው ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይልም ለፋብሪካዎቹ አስተማማኝና ርካሽ ኢነርጂ በማቅረብ የምርት ወጪን ይቀንሳል።
ማዳበሪያ ማምረት ብቻውን ግብ አይደለም፤ ዋናው ዓላማ የአፈርን ለምነት መጠበቅና የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ነው።
ለዓመታት ከውጭ የሚመጣው ማዳበሪያ የሁሉንም አካባቢ አፈር ባሕርይ ያላገናዘበ በመሆኑ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የአፈር አሲዳማነትን ሲያባብስ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡ ፋብሪካዎች ከሀገራዊ የአፈር ምርመራ ካርታ ጋር በመናበብ፣ ለእያንዳንዱ ወረዳና የአፈር ዓይነት የሚስማሙ ንጥረ-ነገሮችን የያዙ የተቀመሙ ማዳበሪያዎችን ለማምረት ያስችላሉ።
የመደመር መንግሥት የልማት አቅጣጫ የተፈጥሮ ሀብትንና ዕውቀትን በማቀናጀት ከጥገኝነት ወደ አምራች ኢኮኖሚ መሸጋገርን ዋነኛ ግቡ አድርጓል።
እንደ ስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ሁሉ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታም የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።
ይህ ጉዞ ሲሳካ ኢትዮጵያ የራሷን ሕዝብ ከመመገብ አልፋ፣ ለቀጣናው ገበያ የግብርና ግብዓትና የምግብ ምርት አቅራቢ በመሆን የኢኮኖሚ ነጻነቷንና ቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ታቆማለች።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: