ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዐረብኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሲቪል ተዋናዮችን ጨምሮ ሁሉም የሱዳን ወገኖች በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እና አመቻችነት በሚካሄደው የ"ሱዳን ለሱዳን" ምክክር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የምክክሩ ዋና ዓላማ ጦርነቱን እና መከፋፈልን በማቆም ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚሆን ብሔራዊ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በግድ የሚጫኑ መፍትሔዎች ዘላቂ ሰላም ስለማያመጡ፣ የሱዳን መጻኢ ዕድል መወሰን ያለበት በራሳቸው በሱዳናውያን ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በዚህም ምክክር አማካኝነት ሰፊ ተቀባይነት ያለው የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንደሚመሠረት፣ የፈረሱ የመንግሥት ተቋማት መልሰው እንደሚገነቡ እንዲሁም የሀገሪቱ አንድነት፣ ብዝኅነት እና ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት አዲስ ብሔራዊ ውል እንደሚቀረጽ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
አራተኛ ዓመቱን የያዘው የሱዳን ጦርነት በሰው ሕይወት፣ በመሠረተ ልማትና በመንግሥት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንና ሰፊ መፈናቀልን ማስከተሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ጦርነቱ መቀጠሉ ማንንም እንደማይጠቅም እና ትልቁ ኪሳራ የሚደርሰው በሱዳን ታሪክ እና ተቋማት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ እውነተኛው አሸናፊ ሱዳንና ሕዝቧ ሊሆኑ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት ከጂኦግራፊና ከፖለቲካ ባሻገር በጥልቅ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ እ ና ባህላዊ ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የሱዳን ሰላም ከኢትዮጵያ ሰላም የማይነጠል እና ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም ስትጥር ይህ የመጀመሪያዋ አለመሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በ2011 ዓ.ም ከሱዳኑ ታኅሣሥ አብዮት በኋላ በሲቪሉና በወታደራዊው ክንፍ መካከል ስምምነት እንዲደረስ መንገድ መክፈቷን አስታውሰዋል።
አሁንም ኢትዮጵያ ከማንኛውም የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት በጸዳ መልኩ ከሁሉም ወገኖች እኩል ርቀት ላይ በመቆም፣ ግልጽነት እና መከባበር የሰፈነበት የምክክር መድረክ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ወዳጅ ሀገራት እና ቀጣናዊ ተቋማት ግጭቱን ከሚያራዝሙ ጠባብ የፖለቲካ ስሌቶች በመራቅ ከሱዳን ሕዝብ ጎን እንዲቆሙና ሰብዓዊ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያም በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን ተጠቅማ ለሱዳን አንድነትና መረጋጋት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል እና ውይይት ወደ ሰላም የሚያሻግር ድልድይ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎቷ መሆኑን አስታውቀዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: