ለአምስት አሥርት ዓመታት በፍለጋ ብቻ ታጥሮ የቆየው የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ዛሬ ታሪኩን እየቀየረ ያለው በጥሬው ወደ ውጭ ተጭኖ ዶላር በማምጣት ብቻ አይደለም።
በየዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሚበላው የማዳበሪያ ምርት ግብዓት በመሆን፣ ለከተማ አውቶቡሶች የኢነርጂ ጉልበት በመስጠት እና የሴራሚክ ፋብሪካዎችን የነዳጅ ወጪ በ40 በመቶ በመቀነስ ከአርሶ አደሮች ጓዳ እና ከከተሜው የዕለት ኑሮ ጋር በቀጥታ እየተሳሰረ ይገኛል።
ይህ አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሀብቷን ከሀገር ውስጥ ልማት ጋር በማስተሳሰር የጀመረችውን ጥልቅ ስትራቴጂያዊ ለውጥ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
አዲሱ የኢኮኖሚ ስሌት የውጭ ምንዛሪን እያመነጨ በተመሳሳይ ጊዜ የገቢ ምርት ጥገኝነትን የሚሰብር ባለሁለት ስለት መንታ የኢኮኖሚ ሞተር ነው።
በአንድ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና የብሔራዊ ባንክ የዋጋ ማስተካከያ የኮንትሮባንድ ሰንሰለትን በመስበሩ፣ የወርቅ ወጪ ንግድ ገቢ ከ350 ሚሊዮን ዶላር ወደ 5.7 ቢሊዮን ዶላር ተስፈንጥሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከወጪ ንግድ ባልተናነሰ ኢኮኖሚውን እየታደገ ያለው የገቢ ምርት መተካት ስትራቴጂ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከምንጩ እየገደበ ነው።
ኢትዮጵያ ለድንጋይ ከሰል ታወጣ የነበረውን 300 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ ማስቀረቷ እና በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቀውን ብረት በሀገር ውስጥ ለማምረት መነሳቷ፣ ማዕድን የበጀት መደጎሚያ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ነፃነት ዋስትና መሆኑን ያረጋግጣል።
የከርሰ ምድር ሀብትን እሴት ሳይጨምሩ በጥሬው መቸብቸብ ለሀብት እርግማን እንደሚዳርግ የዓለም ተሞክሮ ያመላክታል።
ኢንዶኔዥያ ጥሬ ኒኬልን አግዳ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማዕከል እንደሆነችው፣ ቦትስዋና እና ኖርዌይም አልማዝና ነዳጃቸውን በጠንካራ ተቋማት እና በመንግሥት እና በግል አጋርነት ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ጋር እንዳስተሳሰሩት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረች ነው።
ለ30 ዓመታት በጥሬው ሲላክ የነበረውን ታንታለም በሀገር ውስጥ ማቀነባበር፣ የአፋርን ግዙፍ ፖታሽ ማልማት እና በሊቲየም ሀብቷ ወደ ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ኢነርጂ ሰንሰለት መግባት የዚሁ ሽግግር ማሳያዎች ናቸው።
ይህም እ.አ.አ በ2030 የማዕድን የወጪ ንግድን ከ10 ቢሊዮን ዶላር በማሻገር ለጠቅላላ ምርት የ10 በመቶ ድርሻ እንዲያበረክት እና ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ አምስት አምራቾች ተርታ እንድትሰለፍ የሚያስችል ጉዞ ነው።
ይሁንና የተፈጥሮ ማዕድን የማይተካ የአንድ ጊዜ ብቻ ስጦታ በመሆኑ፣ ይህ ሽግግር ዘላቂ የሚሆነው በጠንካራ ተቋማዊ መሠረትና ግልጽነት ላይ ሲቆም ብቻ ነው።
የኮንትሮባንድ መረቦችን ከጊዜያዊ የዋጋ ማበረታቻ ባለፈ በዘላቂ የሕግና የዲጂታል ቁጥጥር መዝጋት፣ በማዕድን አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚነት እና የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶችን በማክበር እውነተኛ የማኅበረሰብ ቅቡልነትን ይበልጥ ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ከዚህም ባሻገር ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ ሲገቡ ለኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እና ባለሙያዎች ተጨባጭ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር መፍጠር ይገባል።
እነዚህ ምሰሶዎች በጽናት እና ሳይሸራረፉ ከተጠበቁ፣ የከርሰ ምድር ሀብታችን ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ብልጽግናን በመገንባት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነፃነት ታሪካዊ ድልድይ ይሆናል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: