በኦሮሚያ ክልል አስደናቂ እመርታ እያስመዘገበ የሚገኘው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ቀደም ሲል በጥቂት ሄክታር መሬት ላይ ብቻ በባህላዊ መንገድ ይመረት የነበረውን የሩዝ ምርት በኩታ ገጠም አስተራረስ እና በዘመናዊ ግብዓቶች በማስፋፋት፣ ክልሉን የሩዝ ምርት ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ይህ ኢኒሼቲቭ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ እንዳሻው ጀማነህ እንደገለጹት፣ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ገቢ የሚያሳድጉ ስትራቴጂያዊ ሰብሎች ላይ በተሠራው ሥራ፣ አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው።
ክልሉ ለሩዝ ልማት ተስማሚ ሥነ-ምህዳር ቢኖረውም ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ፣ እስከ 2013/14 የምርት ዘመን ድረስ ይለማ የነበረው መሬት ከ16 ሺህ ሄክታር እንዳልበለጠና የሚገኘው ምርትም እስከ 805 ሺህ ኩንታል ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ ግን የክልሉ መንግሥት በሩዝ ልማት ውጤታማና አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት ኢኒሼቲቩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተለይም በምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የሩዝ ልማቱ እየተስፋፋ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በክልሉ የሩዝ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የግብዓት አቅርቦት እንዲሳለጥ ከመደረጉም ባለፈ፣ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አቶ እንዳሻው ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት የተቀረጹ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የሩዝ ልማት ባለፉት ዓመታት ትልቅ እመርታ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከለማው የሩዝ ሰብል ወደ 63 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን አንስተዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከለማው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ እስካሁን ከ544 ሺህ 607 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሩዝ ሰብል መሰብሰቡን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አርሶ አደሮቻችንም የደረሰውን የሩዝ ሰብል ወቅቱን ጠብቀው በኮምባይነር እና በባህላዊ የአሳባሰብ ዘዴ ከሰበሰቡ በኋላ በድህረ ምርት የሚፈጠረውን ብክነት በመቀነስ ላይ አጥብቀው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: