Search

ሁለተኛው የአፍሪካ ፊልም ገበያ እና ሽልማት መድረክ (AAFMA 2026) በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ማክሰኞ ኅዳር 15, 2019 38

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በኢትዮ-አርክውድ ኢንተርቴይመንት አ.ማ ጥምረት የተዘጋጀው ሁለተኛው የአፍሪካ ፊልም ገበያና ሽልማት መድረክ (AAFMA 2026) ከኅዳር 18 እስከ 19 ቀን 2019 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

መድረኩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ የመደመር መንግሥት በፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ተደራሽ የሚሆኑበት ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፊልም ፕሮዳክሽን እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ኪነ-ጥበብ ሀገራዊ እሴቶችን እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ፣ አፍሪካውያን በራሳቸው አንደበት ታሪካቸውን በመተረክ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም እንዲሁም የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን (PPP) ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

“የአፍሪካን ኦዲዮቪዥዋል ኢንዱስትሪ ሥርዓት መገንባት፡ ከዕቅድ ወደ ተግባር” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ከ500 በላይ ባለሙያዎች ይታደማሉ።

በሁለቱ ቀናት ቆይታ በፖሊሲ እና ሕግ ማዕቀፎች፣ በብሪቲሽ ኤምባሲ ድጋፍ በሚካሄድ የሴቶች የፊልም ተሳትፎ፣ በኢትዮጵያ የፊልም ትምህርት አቅጣጫ እንዲሁም የአፍሪካን ታሪኮች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ዙሪያ የሚመክሩ አራት ዋና ዋና የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ የኢትዮ-አርክውድ ኢንተርቴይመንት ተወካይ ወ/ሮ አርሴማ ወርቁ ገልጸዋል።

ከዋናው መድረክ አስቀድሞም ከኅዳር 14 እስከ 17 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲኒማ ኮምፕሌክስ የጥበብ ጋለሪ በብሪቲሽ ካውንስል ድጋፍ የአራት ቀናት የፊልም ኮስትዩም ዲዛይን ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

የአፍሪካን የፈጠራ ሀብት ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድልና የኢንቨስትመንት ትስስር በሚቀይረው በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ የፊልም እና የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የትምህርት ተቋማትና መላው ጥበብ ወዳድ ሕዝብ እንዲገኙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: