በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የተሻሻለው የከተማ ልማት ፖሊሲና የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ ከተሞችን ከድህነት እና ኢ-መደበኛ ፍልሰት ማዕከል ስጋትነት አውጥተው ወደ ፈጠራ፣ ኢንዱስትሪ እና ብልጽግና ማዕከልነት እየቀየሯቸው መሆኑን የዘርፉ ምሁራንና የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ።
መንግሥት የከተሞችን እምቅ ፀጋዎች ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊ ትሥሥር እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር አቀናጅቶ የመገንባት ስትራቴጂ መከተሉ፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የከተማ ልማት ተምሳሌት እያደረጋት ይገኛል።
በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ከተሞች ፕሮግራም መሪ ያሬድ ተሾመ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አዲሱ ፖሊሲ በከተሜነት ላይ ሲንጸባረቅ የነበረውን የቆየ አመለካከት በመሠረቱ መቀየሩን ተናግረዋል።
ከተሞችን እንደ ሥርዓት አልበኝነት እና ድህነት መናኸሪያ ከማየት ይልቅ፣ እንደ ኅብረ-ብሔራዊነት፣ ፈጠራ እና ኢንዱስትሪ መዳረሻ እንድናያቸው ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣቱንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ከሚስተዋለው አጠቃላይ ፍልሰት ውስጥ 63.2 በመቶ የሚሆነው በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ማለትም በሥራ ፍለጋ የሚከሰት ሲሆን፣ 23 በመቶው ለትምህርት፣ ለጋብቻ እና ለማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ቀሪው 13.8 በመቶ ደግሞ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚፈጠር ነው።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት እና የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ እንደ አዳማ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ እና ጅማ ባሉ ዋና ዋና የክልል ከተሞች መስፋፋቱ፣ ዜጎች ወደ ዋና ከተማዋ ከመፍለስ ይልቅ ባሉበት አካባቢ ሠርተው እንዲለወጡ እና የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማት ዋና ዋና መንገዶችን፣ የባቡር መስመሮችን እና የወንዝ ዳርቻዎችን መሠረት በማድረግ ከተሞችን ውብ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎች ተደራሽ የማድረግ ሁለንተናዊ ሥራ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ የልማት አቅጣጫ በክልል ከተሞች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማነቃቃት ያልተመጣጠነ ፍልሰትን በተጨባጭ እየገታ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁን እየተከናወነ ያለው የከተማ ልማት ከተሞችን ከማዘመን ባለፈ፣ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ የማሸጋገር ዓላማን አንግቧል።
ዶ/ር ዳንኤል እንደ ምሳሌ እንዳነሱት የመስቀል አደባባይና የሆራ ፊንፊኔ ባህላዊ እሴቶች፣ እንዲሁም የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የእንጦጦ ፓርክ፣ ከዘመናዊ የከተማ ፕላን ጋር ተዋህደው የትውልድ ዐሻራን እንዲያስቀጥሉ ተደርገው የተገነቡ ናቸው።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የተቀናጀ የከተማ ልማት ከተሞችን ለኑሮ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ተመራጭ በማድረግ፣ የቱሪዝም ገቢን በማሳደግ እና ሥልጡን እንዲሁም ተወዳዳሪ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: