Search

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም እያሳየች ነው፡- ዶክተር መቅደስ ዳባ

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 61

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ሲሆን፣ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የጤና ሚኒስትሯ ከጤናው ዘርፍ ባሻገር የገንዘብ፣ የዕቅድ፣ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፎችን የወከሉ ከ46 በላይ ሚኒስትሮች በጉባኤው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ታዳሚዎች የኢትዮጵያን ውጤታማ ተግባርና ተሞክሮ እንዲሁም ከጤናው ዘርፍ ባለፈ በሌሎችም መስኮች እያስመዘገበቻቸው ያሉ ሁለንተናዊ ለውጦች መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ይህም ሀገራችን ያላትን የመሥራትና የመፈጸም አቅም በተግባር በማሳየት በአህጉሪቱ ላይ እምነት እንዲጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ አጋሮችና የግል ድርጅቶች በጋራ እየተወያዩበት ባለው በዚህ መድረክ፣ ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ያከናወነቻቸውን ሥራዎች በተለያየ መንገድ እያቀረበች ትገኛለች ብለዋል።

ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ እና በሕክምና ሪፈራል ሥርዓት የሠራቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች መመልከታቸውን አስረድተዋል።

በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የማኅበረሰቡን ጤና በዲጂታል መንገድ የሚከታተሉበትን የኤሌክትሮኒክ የማኅበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት በተግባር ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ሞዴሎችና የዲጂታል አሠራሮች በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት ማሳየታቸውንና የልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የዓለም የጤና አስተዳደር ሥርዓት እየተቀየረ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ኢትዮጵያ የጤና ዲፕሎማሲን በስፋት እየተጠቀመች መሆኗን ተናግረዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ወደ ተጨባጭ ውሳኔዎች የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸው፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና ውይይቶችና በሳይንስ ትግበራዎች ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪም ሆና እየወጣች መሆኗን አስረድተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተከታታይ የተካሄዱት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎች ለዚህ መድረክ ስኬት መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: