ታላቁ የኦዳ ዛፍ፣ የጥበብ፣ የፍትሕ እና የዕርቅ ሕያው መንበር ነው። ቅርንጫፎቹን በሰፊው የዘረጋው ይህ ታሪካዊ ዛፍ፣ ከሥሩ ለሚጠለሉት ሁሉ የማዕረግ እና የክብር ድንኳን ሆኖ ቆይቷል።
የፀሐይ ብርሃን በኦዳው ለምለም ቅጠሎች መሐል ሰተት እያለ ሲያበራ፣ ከሥሩ የተሰበሰቡት አባ ገዳዎች ግርማ ሞገስ አካባቢውን ይሞላዋል።
ነጭ የሀገር ባህል ልብሳቸውን ለብሰው፣ በግምባራቸው ላይ የክብር እና የኃላፊነት መገለጫ የሆነውን ከላቻ አስረው፣ በእጆቻቸው ደግሞ የሥልጣን፣ የሕግ እና የፍትሕ ምልክት የሆነውን ቦኩ ጨብጠው በግርማ ሞገስ ይታያሉ።
ይህ ሥፍራ የፍርድ አደባባይ አይደለም፤ ይልቁንም የልብ ቁስል የሚፈወስበት፣ በቀል በይቅርታ የሚሸነፍበት እና የተበጠሰ የፍቅር ገመድ ዳግም የሚቀጠልበት ነው።
በዚህ ታላቅ ስፍራ በሚውለው በጉባኤ መሐል የተቀያየሙት እና የተጣሉት ወገኖች ፊት ለፊት ይቀመጣሉ። አባ ገዳዎች የሰላም፣ የእርጥበት እና የልምላሜ ተምሳሌት የሆነውን ጮቆርሳ (ለምለም ሣር) በእጃቸው ይዘው፣ ቦኩአቸውን ወደ ምድር ዝቅ በማድረግ የዕርቅ ሂደቱን በተረጋጋ መንፈስ ይጀምራሉ።
በገዳ ሥርዓት ፍትሕ ማለት ጥፋተኛን በመቅጣት እና በማዋረድ የሚጠናቀቅ ሂደት አይደለም። ይልቁንም፣ አጥፊው ጥፋቱን አምኖ በጥበብ ሲቀጣ እና ሲመከር፣ የተበደለው ደግሞ በአግባቡ ሲካስ እና ይቅር ሲል የሚገኝ እውነተኛ የነፍስ እና የኅሊና ዕረፍት ነው።
የሽምግልናው ቃል ተሰምቶ፣ ውሳኔው በሁለቱም ወገኖች ዘንድ በጸጋ ተቀባይነት ሲያገኝ፣ አስደናቂው የምስጋና እና የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ይከተላል። አባ ገዳዎች እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ።
በኦዳው ዛፍ ሥር "ነጋ ሃ ተኡ... ነጋ ሃ ተኡ... ነጋ ሃ ተኡ…" (ሰላም ይሁን፣ ሰላም ይሁን፣ ሰላም ይሁን) የሚለው የአባ ገዳዎቹ የምርቃት ድምፅ ያስተጋባል። ለምድር፣ ለሰው ልጅ፣ ለከብቱ፣ ለሰብሉ፣ እንዲሁም ለሀገር ሰላም እና በረከትን ይለምናሉ።
ያኔ ቁጣ ይበርዳል፤ ትናንት የተጣሉት እና ቂም የቋጠሩት ሰዎች እጅ ለእጅ ተጨባብጠው፣ ተቃቅፈው በይቅርታ አዲስ ምዕራፍ ይጀምራሉ።
ይህ በኦዳ ዛፍ ሥር የሚከናወነው የዕርቅ እና የፍትሕ ሥነ-ሥርዓት፣ የገዳ ሥርዓት የሰው ልጅ በእኩልነት፣ በፍትሕ እና በመከባበር እንዴት በሰላም መኖር እንዳለበት የሚያስተምር፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም የተበረከተ የቀደምቶቻችን ሕያው የዴሞክራሲ እና የጥበብ ስጦታ ነው።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: