"የማይበገር ንግድ እና ዘላቂ የእሴት ሰንሰለቶች" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ባለው 15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ ላይ፣ በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኙ ላኪ ድርጅቶች ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ኮንፈረንስ ከኅዳር 15 እስከ 16 ቀን 2019 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ይቆያል።
በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢን ጨምሮ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አምባሳደሮች ተሳትፈዋል።
በቅባት እህሎች ዘርፍ 24.45 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ያስመዘገበው በላይነህ ክንዴ ግሩፕ አንደኛ በመሆን ተሸልሟል።
12.38 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው አልያንስ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ ሁለተኛ፣ እንዲሁም 11.63 ሚሊዮን ዶላር ያስመዘገበው ዐቢይ ማስረሻ (ግሽ ማር ቢዝነስ) ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ተሸልመዋል።
በጥራጥሬ ዘርፍ ደግሞ 35.16 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ያስገኘው አብርሃም አበበ ኢምፖርት ኤክስፖርት አንደኛ ሆኗል።
34.61 ሚሊዮን ዶላር ያስመዘገበው ኤም ኤስ ኤ ትሬዲንግ ሁለተኛ፣ እንዲሁም 12.76 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ላምፕሮስ ትሬዲንግ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: