የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በዩራነስ ዙሪያ የምትሽከረከር አዲስ ጨረቃ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
በዩራነስ ፕላኔት ዙሪያ ከዚህ ቀደም የሚታወቁ 28 ጨረቃዎች ሲኖሩ፣ አዲሱ ግኝት አጠቃላይ በፕላኔቷ ዙሪያ ያሉ ጨረቃዎችን ቁጥር ወደ 29 ከፍ አድርጎታል።
አዲሷ የዩራነስ 29ነኛዋ ጨረቃ ለፕላኔቷ በጣም ቅርብ ከሆኑት ትናንሽ ጨረቃዎች 14ኛዋ መሆኗ ተገልጿል።
ሳይንቲስቶች በጊዜያዊነት 'ኤስ/2025 ዩ1' የሚል ስያሜ የሰጧት ጨረቃዋ፤ የዩራነስ ቀለበቶች እንዴት እንደተፈጠሩ እንዲሁም ተጨማሪ የተደበቁ ጨረቃዎችን ለማግኘት ፍንጭ ታሳያለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ናሳ ባወጣው መረጃ ገልጿል።
ከፀሐይ ባላት ርቀት ሰባተኛዋ ፕላኔት ዩራነስ 13 ደብዛዛ ቀለበቶች ያሏት ግዙፏ በረዷማ ፕላኔት ናት፡፡
ፕላኔቷ እ.አ.አ በ1781 በእንግሊዛዊው አስትኖመር ፍሬዴሪክ ዊሊያም ኸርሻል ነበር የተገኘችው።
በሴራን ታደሰ