Search

የ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሕክምና በነፃ የሰጠው የቱርኪዬ የሕክምና ቡድን

ዓርብ ነሐሴ 16, 2017 159

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሼህ ሀሰን የበሬ ሪፈራል ሆስፒታል ለ1 ሳምንት የቆየ ነፃ የጉልበትና የዳሌ አጥንት ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል።

ከቱርኪዬ በመጣ የሕክምና ቡድን የተሰጠው እያንዳንዱ ቀዶ ሕክምና ከ300 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ የሚጠይቅ እንደነበር ተገልጿል።

በሕክምና ቡድኑ የሽኝት መርሐ-ግብር ላይ የተገኙት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሀመድ፥ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎች የተሰጠው ነፃ የሕክምና አገልግሎት በርካቶችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ነፃ የሕክምና አገልግሎቱ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ያግዛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከቱርኪዬ በመምጣት አገልግሎቱን ለሰጠው የሕክምና ቡድን ምስጋና አቅርበዋል።

በ1 ሳምንት ውስጥ ለ34 ዜጎች ሙሉ ቀዶ ሕክምና የተሰጠ ሲሆን፤ ሰው ሰራሽ የጉልበትና የዳሌ አጥንት ገጠማም መካሄዱን የሕክምና ቡድኑ መሪ ዶ/ር አብዱላሂ ባልቺ ተናግረዋል።

የሕክምና ቡድኑ አባላት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ነፃ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ነፃ የሕክምና አገልግሎቱን ያገኙ ዜጎችም ሕክምናው የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ እና ድካም ያስቀረላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

#ኢቢሲዶትስትሪም #ኢቲቪ #ቱርኪዬ #ኢትዮጵያ #ጅግጅጋ