የኩላሊት ጠጠርን ያለቀዶ ጥገና ስቃይ በቀላሉ ለማስወገድ የተሰራው አነስተኛ ሮቦት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣቱን የካናዳው ዋተርሉ ዩኒቨርስቲ አስታውቋል።
የካናዳ፣ የስፔን እና የጀርመን ሳይንቲስቶችን ያካተተው የተመራማሪዎች ቡድን ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው፤ በዓለም ላይ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የህመም ምክንያት የሆነውን የኩላሊት ጠጠር ለማስወገድ የተሰራው ሮቦት የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ፈጽሟል።
በመጠኑ የአንድ ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አነስተኛ ሮቦት በሽንት ትቦ ውስጥ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በሕክምና መቆጣጠሪያ መሳሪያ አማካኝነት የኩላሊት ጠጠሩ ወደሚገኝበት ቦታ እንዲደርስ ይደረጋል ሲል የምርምር ቡድን አስረድቷል።
ከዚያም የኩላሊት ጠጠሮቹን ማሟሟት የሚችል ኢንዛይም በመልቀቅ በቀናት ውስጥ የጠጠሮቹን መጠን አሳንሶ በሽንት መልክ መወገድ እንዲወገዱ ያደርጋል ተብሏል።
በዓለም ላይ ከመቶ ሰዎች መካከል በአስራ ሁለቱ ላይ እንደሚከሰት ጥናቶች የሚያመላክቱትን የኩላሊት ጠጠር ሕመም ለማከም መፍትሄ ይሆናል የተባለለት ይህ አነስተኛ ሮቦት በቀጣይ በትላልቅ እንስሳት ላይም እንደሚሞከር ተገልጿል።
ከዚያም የሰው ልጅን ለማከም እንደሚውል የተገለፀ ሲሆን እስካሁን ባለው ደረጃ ግን ምርምሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በካናዳው ዋተርሉ ዩኒቨርሲቱ የሚገኙት ተመራማሪዎች አመላክተዋል።
በዋሲሁን ተስፋዬ