መነሻው ቀላል ነው፡፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፡፡ “UTI” ይሉታል የጤና ባለሙያዎች፡፡
ለዚህ ምርመራ ነበር ታካሚዋ ጤና ጣቢያ የሄደችው፡፡
ቢሆንም ግን ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኑ ተጨማሪ ሌላ ዱብዳ ተነገራት፡፡
ስለዚህም ተጨማሪ ምርመራ እና ሕክምና እንድታገኝ ወደ አለርት ሆስፒታል ተላከች፡፡
ምርመራው ቀጠለ የሲቲ ስካን ምርመራ፡፡ ውጤቱ ደረሰ፡፡ የሽንት ቱቦው ኢንፌክሽኑም ዳነ፤ ተረሳና ሌላ ጭንቀት፡፡ ከኩላሊት ከፍ ብሎ ካለ ሆርሞን አመ የሰውት ክፋል ላይ የወጣ ጤነኛ ያልሆነ እጢም ተገኘ::
ሰላም አበበ (ስሟ የተቀየረ) ትባላለች፡፡ ጤነኛ ያልሆነ እጢ አለብሽ ተብላለች፡፡ ያውም በሆድ ውስጥ፤ያስጨንቃል፡፡ የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ ገና በ30 ዓመት ዕድሜዋ። ያላት አማራጭ ደግሞ ሆዷ ተቀዶ እጢው መውጣት ብቻ ነው፡፡
ካልሆነ እጢውም ይጨምራል፡፡ ካንሰርም ሊሆን ይችላል፡፡ በሕይወቷም ከባድ ችግር ይፈጥራል። ይህ እጢ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ሆርሞኖችን ከሚያመነጭ አድሬናል እጢ ላይ ነው የወጣው፡፡ እጢውም የሚገኘው ቀዶ ህክምናን ፈታኝ በሚያደርግ ቦታ በኩላሊት እና በጉበት መሃል፡፡ በኩላሊት በስተአናት፡፡ በቀኝ ጎን፡፡
አለርት ሆስፒታል የኢንዶክራይን ቀዶ ህክምና ሰብ ስፓሺሊስ አልነበረም፡፡ ስለሆነም ታካሚዋ ለተሻለ ህክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሪፈር ተባለች። ሰላም ሰላም ትሆን ዘንድ ከጡት እና ኢንዶክራይን ቀዶ ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት እንዲሁም የቀዶ ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የህክምና ትምህርት ዲን የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን አምታታው ያስፈልጓት ነበር፡፡ ተመረመረች፡፡
ዶክተር ወንድወሰን አምታታው ይናገራሉ።
“ሰላም እንደመጣች ከኢንዶክሮኒሎጂስት ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ጋር ሆነን ምርመራ አደረግንላት፡፡ ዕጢውም ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገው ወሰንን፡፡ ከቀዶ ጥገናው በፊት ግን ተጨማሪ ምርመራዎች ማሰራት ግድ ይሉ ነበር፡፡ ቢሆንም አልተሰራም፡፡ ሰላም እነዚያን ምርመራዎች ማድረግ አልቻለችም፡፡ ብዙው ምርመራ ሀገር ውስጥም የሉም፡፡ ያሉትም ምርመራዎች በጣም ውድና የታማሚዋ አቅም የሚፈታተን ነበር፡፡ ከቀዶ ሕክምናው በፊት ሜታኔፍሪን፣ ኖርሜታኔፍሪን፣ ሬኒን… የተባሉ የሆርሞን ምርመራዎች ልታሰራ ይገባል፡፡ ቢሆንም ታማሚዋ አቅሟ አልቻለም፡፡ አላሰራችም፡፡ አታሰራም፡፡ ያስጨንቃል”፡፡
ሌላም ጭንቀት አለ፡፡ ከሰመመንና ፅኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ሐኪሞች ጋር ሌላ ምክክር ተደረገ። የሰመመን ህክምና ቡድንም መከረ ።በመጨረሻም ለታካሚዋ ተነግሯት Risk ወስደን ቀዶ ህክምናውን እንስራው ብለን ወሰንን። ሌላ አማራጭ አልነበረም። ታካሚዋም ስለ ሁሉም ነገር ተነገራት። ሰላምም “ፈጣሪ ያውቃል በውሳኔዎቻችሁ ሁሉ እስማማለሁ” አለች።
ቀጣዪ ጥያቄ ምን አይነት ቀዶ ህክምና? የሚለው ነው፡፡ ይህን እጢ ለማውጣት የተለመደው ህክምና ትልቅ የሆድ ቀዶ ህክምና ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቀዶ ህክምና ሆድ በመቅደድ ከሆነ ሰርጀሪው የሚጀመረው ከላይ ሆዷ ጀምረን በቀኝ ሆዷ መጨረሻ ድረስ መቅደድ ይኖርብናል፡፡ ይህም ከባድ ሰርጀሪ እና ረዘም ላለ ጊዜ የህመም ስቃይ ያለው ሲሆን በተጨማሪም ትልቅ ጠባሳ በሆዷ ላይ ጥሎ ያልፋል፡፡ ለአንዲት ለ30 አመት ሴት ይህንን ስቃይና ትልቅ ጠባሳ መተው በጣም ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህ ምን አማራጭ አለ ብለን አሰብን፡፡ ይላሉ የጡት እና ኢንዶክራይን ቀዶ ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተር ወንደሰን አምታታው፡፡
ሆድ ሳይከፍቱ የአድሬናል ዕጢ ቀዶ ሕክምና
ዶክተር ወንድወሰን ስለ ሕክምናው ሲናገሩ የአድሬናል ላፖራስኮፒክ ቀዶ ህክምና ትንንሽ ቀዳዳዎችን (ከአንድ ሳንቲም ባልበለጡ ለመሳሪያ ማስገቢያ ከ3-4 በሆኑ ቀዳዳዎች) በመፍጠር ካሜራና ለቀዶ ህክምና የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች በመክተት ቀዶ ሕክምናውን መሥራት የሚያስችል ነው።
ይም የረቀቀ የሕክምና ጥበብን የሚፈልግ እና ለታካሚዋ አጅግ በጣም የተሻለ ዘመናዊ የህክምና አማራጭ ነው ይላሉ፡፡ ዘመኑን የዋጀውን ቀዶ ሕክምና እንደ ተቋም በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ማድረግ አንችላለን ባለሙያም አለ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የኢንዶክሪንና ጡት ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስታቸውን በህንድ ሀገር የተማሩት ዶክተር ወንድወሰን አምታታው፡፡
እንዲህ ያለ ቀዶ ሕክምናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአደጉት ሀገር ተመራጭ ሆኖ ይሰራል፡፡ ቀዶ ህክምናው ሆርሞን የሚያመነጭ ዕጢ ላይ እንደመሆኑ መጠን እጢው ሲቆረጥ ደም ይፈሳል፡፡ ስለዚህ በአንዴ እጢውን ቆርጠን እንዲሁም ደም እንዳይፈስ የተቆረጠው ቦታ ላይ ቆንጥጠው የሚይዙ ሀርሞኒክ ወይም ላይጌቸር የተባሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች እጅግ አስፈላጊና ያለ እነዚህ መሳሪያዎች ሰርጀሪውን ማሰብ ከባድ ነበር ይላሉ ዶ/ር ወንድወሰን፡፡ ግን እኛ ጋር ሁለቱም ኖረው አያውቁም የሉንም፡፡ሆኖም ግን ባሉን መሳሪያዎች ልንሰራ ወሰንን ይላሉ።
ከኪያም የሕክምና ቡድኑ ተሟላ፡፡ አስፈላጊና አቅም የፈቀደው ሁሉ ነገር ቀረበ፡፡ ሰላም በሰመመን ሐኪሞች እና ረዳቶች ሀገር ሰላም ብላ ተኛች፡፡ ሆዷ ላይ አራት ቦታ መጠነኛ ቀዳዳ ተደረገላት። ከዚያም በካሜራ ታግዘን በስክሪን እያየን ቀዶ ህክምናውን ጀመርን ከአሁን አሁን አቁሙ የሚሉ አንደበቶችን ከሰመመን ሀኪሞቹ ለመስማት ጥረት በማድረግ። ሆኖም ግን ቀጥሉን ብቻ በመሰማት ሁለት ሰዓት የፈጀ ቀዶ ሕክምና ተደረገ፡፡
ቀዶ ሕክምናውም ተሳካ፡፡ በጥቂት ቀዳዳዎች እና ለአይን በማይታዩ ጠባሳወች ያ እጢ ተወገደ፡፡ እናም በክፍሉ ደስታ ሆነ፡፡ ሰላምም ከሰመመን ነቃች ከኦፕራሲዮን ቴብልም ወደ ማገገሚያ ክፋል ተዛወረች። ፈጣሪም ረዳት።
በሕክምና አገልግሎቱ 102 ዓመት ላስቆጠረው የካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የመጀመሪያ የሆነው የላፖራስኮቲክ አድሬናሌክቶሚ (ሆድ ሳይከፈት ቀዶ ሕክምና) በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ የወጣውም እጢም ወደ ኦንኮ ፓቶሎጅ ተላከ የተላከውም ውጤት ከሶስት ቀናት በኃላ ደረሰ፡፡ ካንሰር አይደለም ካንሰር የሌለው እጢ መሆኑም ተረጋገጠ። ትልቅ ብስራት ለተጨነቀችው የ30 ዓመቷ ወጣት። ዛሬ ሰላም ሰላሟን አግኝታ ፈጣሪዋን በማመስገን ላይ ትገኛለች።
ቀዶ ሕክምናውን በበላይነት የመሩት የጡት እና ኢንዶክራይን ቀዶ ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት እንዲሁም የቀዶ ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰን አምታታው በሕክምናው የተሳተፉት የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፍፁም ተረፈ-ጠቅላላ፣ አንሰቲዚሎጅስት ዶክተር ያለው ሁሴን እና ቡድኑ፣ ዶክተር ዳንኤል ዶር ጌታቸው ረዚደንት ሕኪሞች፣ አቶ ደረሰ ቶላ-ትሬንድ ላፓራስኮፒክ ስክረብ ነርስ እና ቡድኑ ስለሁሉም ውጤት ፈጣሪን እመስግነው የሕክምናው ስኬት አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል።
መረጃውን ያደረሰን የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ታካሚዋ ከሕክምናው በኋላ በዓይን የማይታይ ጠባሳ ያክል ሽሮላት ድና መደቤቷ መሄዷን አሳውቋል።