በአሁኑ ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምህዳር ውስጥ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከታሪካዊ ሥረ-መሠረቱ ወጥቶ የብሔራዊ ጥቅም ከፍ ባለ የብልሃት ማዕቀፍ ወደ ማስከበር የተሸጋገረበት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤትን በማስተናገድ ረገድ የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ አዲስ አበባን የመላው አፍሪካ የፖለቲካ፣ የሰላም እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
የመደመር መንግሥት ይህንን የዘመናት ታሪካዊ ርዕይና አርበኝነት መነሻ በማድረግ፣ ዲፕሎማሲን ከመደበኛ የሁለትዮሽ የፕሮቶኮል ግንኙነት አልፎ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የደህንነት ድል ውጤቶች የሚያሸጋግር ጽኑ አቅጣጫ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ይህ ስትራቴጂካዊ ጉዞ መሰረቱ የታነፀው በገቢር-ነበብ የዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ላይ ነው። ንቁ ተሳትፎን ማረጋገጥ፣ አማራጭ የአጋርነት መስመሮችን ማስፋት፣ ከተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በብልሃት መላመድ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ላይ የፊት አውራሪነት ሚና መውሰድ የመደመር ዲፕሎማሲ የሚከተላቸው ዋና ዋና መርሆዎች ናቸው።
እነዚህ መርሆዎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ከማላቅም በላይ በጉባኤዎች ላይ በመሳተፍ ብቻ ሳይወሰኑ ግንኙነቶቹን ወደ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ኃይል ልማት እና የዜጎች ተጠቃሚነት የሚቀይር ውጤታማ የትብብር አድማስ ዘርግተዋል።
የመደመር ዲፕሎማሲ አንዱና ዋነኛው ምሰሶ "ቅድሚያ ለጎረቤት" የሚለው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ነው። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከፖለቲካ ወዳጅነት ባለፈ በኢኮኖሚ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ በባቡር መስመር፣ በሎጂስቲክስ እና በወደብ ልማት አስተሳስራለች።
የጎረቤት ሀገር መረጋጋት ለኢትዮጵያ መረጋጋት፣ የጎረቤት ኢኮኖሚ መጠናከርም ለኢትዮጵያ ንግድና እድገት ትልቅ በር ነው ከሚለው ጽኑ እምነት በመነሳት በቀጣናው የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ድርድር፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት ታሪካዊ ርምጃዎች ተወስደዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የባህር በርና የወደብ መዳረሻ ጥያቄ ከንግድ ፍላጎት ባለፈ ከኢኮኖሚ ደህንነት፣ ከቀጣናዊ ትስስር እና ከረጅም ጊዜ ልማት ጋር የተቆራኘ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ቅቡልነትን ያገኘ እና የማይቀለበስ የሰርክ አጀንዳ ሆኖ በድል እየተመራ ይገኛል።
በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክም ኢትዮጵያ ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗ ከተለያዩ የዓለም ኢኮኖሚ ማዕከላት ጋር ያላትን ትስስር ያጠናከረ ሲሆን፤ በአዲስ ልማት ባንክ (NDB) አማካኝነት ለመሰረተ ልማት የሚውል ፋይናንስ ለማግኘት፣ አገራዊ ገንዘቦችን በንግድ ስልት በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ እና ከግሎባል ሳውዝ (Global South) ሀገራት ጋር አዳዲስ የትብብር አማራጮችን ለመፍጠር አስችሏታል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗን በመጠቀም በአህጉራዊ የሰላም፣ የደህንነት እና የልማት አጀንዳዎች ላይ የምታደርገው መሪ ተሳትፎም የዚሁ ስኬት ማሳያ ነው።
የመደመር መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበው ስኬት ከባህላዊ ምላሽ ሰጪ አቀራረብ ወጥታ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም በግልጽ የምታስጠብቅበት፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ የምትለማበት እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በባለቤትነት የምትመራበትን የድል ከፍታ ላይ አድርሷታል።
ይህ የታደሰ የታሪክ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ በህብረትና በጽናት የተራመደ #ትልቅሕዝብ እና ለዓለም አቀፍ ድል የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
ታሪካዊ ክብሯን በዘመናዊ የትብብር አድማስ አጠናክራ የቀጣናውን ሰላም፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የዜጎቿን የብልጽግና ጉዞ በማረጋገጥ ረገድ አቻ የማይገኝለት አሸናፊ የውጭ ግንኙነት መስመር አስመስክራለች።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: