Search

የግብርና ትራንስፎርሜሽን፡- የዜጎችን ሕይወት የመቀየር ሀገራዊ አቅም

ማክሰኞ ጥቅምት 10, 2019 64

በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የሕዝብ ቁጥር ፍላጎት የመሸከም፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር እና ዘላቂ የሕይወት ማሻሻያ የማምጣት አቅም ያለው ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ መሠረት በማድረግ የመደመር መንግሥት የወሰዳቸው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሠረት ላይ በማቆም ወደ ሁለንተናዊ አቅም እንዲሸጋገር እያደረጉት ይገኛሉ።

በዚህም መሠረት ኢኮኖሚው በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይወሰን እንደ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ማዕድን ያሉ ዘርፈ-ብዙ የእድገት ምንጮች እንዲኖሩት ከተደረገበት አቅጣጫ ጎን ለጎን፣ ለዘመናት የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋና ምሰሶ ሆኖ የቆየውን የግብርና ዘርፍ ማዘመንና ከባህላዊ የአመራረት ዘይቤ ማውጣት ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "በምግብ ራስን መቻል የፖለቲካ ነፃነት መሠረት ነው፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ደግሞ የሀገርን ክብርና ነፃነት የማስጠበቅ ያህል ትልቅ ሀገራዊ ግዴታ ነው" ሲሉ እንደሚያስገነዝቡት ሁሉ፣ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተሠሩት ስትራቴጂያዊ ሥራዎች ቃልን ወደ ተግባር የለወጠ ተጨባጭ እመርታ አስመዝግበዋል።

የዚህ ታሪካዊ ስኬት ዋና ማሳያ ደግሞ በበጋ የመስኖ እና በክረምት የመኸር እርሻ የተመዘገበው የስንዴ ልማት ውጤት ነው። ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ለማስመጣት ታወጣው የነበረውን በየዓመቱ የሚቆጠር ቢሊዮን ዶላሮች በላይ ወጪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ የምትችልበት አዲስ ምዕራፍ እንድትጎናፀፍ አስችሏታል።

በስምንት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን በስንዴ ምርት በኩል ከፍተኛ እድገት ተመዝግቧል። በዚህም ከስምንት ዓመታት በፊት ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የማይሻገረው ዓመታዊ የስንዴ ምርት፣ ባሳለፍነው የ2018 በጀት ዓመት በሦስቱም የምርት ወቅቶች በተከናወነው የልማት ሥራ 8.47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት ወደ 317 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል።

ይህ የስንዴ ልማት ስኬት እንደ መነሻ ተወስዶ በአሁኑ ወቅት ትኩረቱ ወደ ሌሎች የግብርና ምርቶች ማለትም ወደ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች እና የእንስሳት ሀብት ልማት እንዲሰፋ ተደርጓል። ከዚሁ ጎን ለጎን የግብርናውን ሜካናይዜሽን ለማፋጠን ዘመናዊ ትራክተሮች እና የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት እንዲስፋፋ በመደረጉ፣ አርሶ አደሩ ከኋላቀር አተራረስ ወጥቶ በሰፊው እንዲያመርት፣ የምርት ጥራት እንዲሻሻልና ብክነት እንዲቀንስ አስችሏል።

የመንግሥት ትኩረት በሀገር ውስጥ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች እና በአቅርቦት ሰንሰለቱ ማሻሻያ ላይ ማተኮሩ አርሶ አደሩ ያለምንም እንግልት ግብዓት እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ፣ የአፈር አሲዳማነትን የሚከላከሉ ጥናቶችና የማስተካከል ሥራዎች ተከናውነዋል።

 ከቡና እና ከንግድ ሰብሎች አኳያም የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ገቢው ከፍ እንዲል የተደረገ ሲሆን፣ እንደ አቮካዶ እና ሙዝ ያሉ ምርቶች በሰፊው ተመርተው ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፍ ገበያ በመቅረባቸው የዜጎችን የኑሮ ደረጃ አሻሽለዋል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የውኃ ማጠራቀሚያዎች እና ጥቃቅን የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተቀናጅተው በመሠራታቸው አርሶ አደሩ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆን በክረምትም ሆነ በበጋ ማምረት የሚያስችል አቅም በመገንባቱ የገጠሩ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲነቃቃ አድርጎታል።

በአጠቃላይ የመስኖ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የሜካናይዜሽን አጠቃቀምን ማሳደግ እና አነስተኛ አቅም ያላቸውን አባወራዎች ወደ አምራችነት ማሸጋገር ቀጣይነት ያለው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ቀጥሏል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት እነዚህ ሁለንተናዊ ሥራዎች ኢትዮጵያ ወደ ግብርና ትራንስፎርሜሽን እያመራች መሆኗን በግልጽ የሚያሳዩ ሲሆን፣ አሁን ላይ የተጣለው ጠንካራ መሠረት ሀገራችን የምግብ ሉዓላዊነቷን አረጋግጣ በአፍሪካ የኢኮኖሚና የምግብ ዋስትና ማዕከል እንድትሆን የሚያስችላትን አስተማማኝ መንገድ ቀይሷል።

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: