በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በሰላማዊ ውይይት እና በቀጣናዊ ትስስር ላይ የተመሠረተ ጽኑ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመከተል ላይ ትገኛለች።
በዚህ መዋቅራዊና አህጉራዊ የታሪክ ሂደት ውስጥ ኤርትራ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትናን፣ ወዳጅነትንና የጋራ ልማትን ማጠናከር ብቸኛውና የሚያዋጣው መንገድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላ ያስመዘገበችውን አጠቃላይ ሁኔታ በስፋት ዳስሰዋል።
ከነፃነት በፊት ደማቅና ውብ የነበሩት የኤርትራ ከተሞች ዛሬ ላይ የፍርስራሽ ክምርና የጉስቁልና መኖሪያ መሳላቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ወዳድና እንግዳ ተቀባይ የነበረው የኤርትራ ሕዝብ ከነፃነት በኋላ የነበረውን ሁሉ አጥቶ እንግልትና ስደት መገለጫው መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ውድቀት ሊከሰት የቻለበት ዋና ምክንያት ሕግደፍ ልማትንና የተቋማት ግንባታን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መሣሪያ ለመሆን በመምረጡ እንደሆነም አብራርተዋል።
ኤርትራን በኢትዮጵያ ላይ እንደ መጠቀሚያ የሚያንቀሳቅሷት የውጭ ኃይሎች ለኤርትራ ሕዝብ የሚበጅ መፍትሔ ሊያመጡ እንደማይችሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ አካላት የራሳቸውንም ችግር መፍታት ያልቻሉ በመሆናቸው “አይዞህ ባዮቹ ጥይት ከማቀበል አልፈው የኤርትራን ችግር ሊፈቱ አይችሉም” ሲሉ አሳስበዋል።
ባለፉት 35 ዓመታት ከታየው ታሪካዊ እውነታ መማር እንደሚገባ በመጠቆም፣ የሚያዋጣው ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትናና አጋርነትን ማጠናከር እንጂ የጠላቶች መናኸሪያ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች #ትልቅሀገር፣ የጋራ እድገትንና አብሮነትን ያቀነቀነ #ትልቅሕዝብ እና ለመላው ቀጠናው መረጋጋት የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር በመሆኗ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመልማት ለምናቀርበው ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ግን መዘዙ እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: