በዓለም አቀፉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምህዳር ውስጥ የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት ስብስብ አባላቱን በማስፋፋትና አዳዲስ አህጉራዊ የትብብር ስትራቴጂዎችን በመቀየስ የደቡበ ዓለም (Global South) ሀገራትን ድምፅ፣ ተጽዕኖ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ይገኛል።
ብሪክስ የዓለም አቀፉን ህዝብ 49.5 በመቶ የሚወክል፣ 40 በመቶ የሚሆነውን የምድር አጠቃላይ ምርት የሚሸፍን እና 26 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ ንግድ የሚቆጣጠር ግዙፍ የጂኦፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ኃይል መሆኑ ተረጋግጧል።
አባል ሀገራቱ ባጸደቁት አዲስ የጋራ መግለጫ መሠረት በሀገራት መካከል በሚደረጉ ንግዶች አገራዊ የምንዛሬ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ ፈጣንና ዝቅተኛ ወጪ ያላቸውን ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ ሥርዓቶች መዘርጋት፣ የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋፋት እና በምግብና በኃይል ደህንነት ላይ የተጠናከረ ትብብር ማድረግ ዋነኛ የፖሊሲ ትኩረታቸው ሆኗል።
ብሪክስ ለታዳጊ ሀገራት የሚያስገኘው ዘርፈ-ብዙ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጠቀሜታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። የብሪክስ ፋይናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ (World Bank) ያሉ የፋይናንስ ተቋማት አሰራር ታዳጊ ሀገራትን በሚመጥን መልኩ ተቃኝተው መዋቅራዊ ማሻሻያዎች እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት (WTO) መመሪያዎችን የሚጥሱ የታሪፍና የንግድ ማቀቢያ እርምጃዎችን በመቃወም፣ የብሪክስ አዲስ ልማት ባንክ (NDB) እና የድንገተኛ መጠባበቂያ ፈንድ ለአባል ሀገራት መሰረተ ልማትና ዘላቂ ልማት ቢሊዮን ዶላሮችን በመመደብ እውነተኛ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ይህ አቅም ብሪክስ የዓለም አቀፍ ሥርዓቱን ሁለንተናዊ ፍትሐዊነት፣ የብዙሃን ተሳትፎ እና አህጉራዊ ትስስርን ለማረጋገጥ የሚከተለው ፍቱን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ መንገድ መሆኑን ያመላክታል።
በዚህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ በአፍሪካ አህጉር ስትራቴጂካዊ የፖሊሲና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ በስብስቡ የተለያዩ ድበር ተሻጋሪ የልማት፣ የንግድና የደህንነት ስራዎች ውስጥ ንቁና በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተች የምትገኝ ሲሆን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ከአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ጋር የሚጣጣሙ የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች።
ሀገራችን በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ በህብረትና በጽናት የተራመደ #ትልቅሕዝብ እና ለዓለም አቀፍ ድል የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር በመሆኗ፣ ከስብስቡ አባላት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማጠናከር፣ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ አህጉራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ የፋይናንስ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የኢንዱስትሪ የማምረት አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ የደቡብ-ደቡብ (South-South) የትብብር መንገዶችን በመዘርጋት ላይ ትገኛለች።
የብሪክስ ስብስብ ከአህጉራዊ ውይይቶች አልፎ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ምርት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የንግድ ፍሰት የተሸጋገረበት ይህ አዲስ ምዕራፍ፣ ለደቡበ ዓለም ሀገራት ትልቅ የልማት ተስፋን ይዞ መጥቷል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ የምታደርገው የነቃ ተሳትፎ እና የምትጫወተው አህጉራዊ የማዕከልነት ሚና፣ የራሷን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሉዓላዊነት ከመገንባቱም ባሻገር፣ ለአፍሪካ አህጉር ዘላቂ ብልጽግና እና ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሚዛን መስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስትራቴጂካዊ መንገድ ሆኗል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: