Search

ሕወሓት ትግራይን እንደ ግል ኩባንያ የተቆጣጠረበት ዘመን አብቅቶለታል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ጥቅምት 10, 2019 60

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕወሓት ትግራይን እንደ ግል ኩባንያ የተቆጣጠረበት ዘመን አብቅቶለታል ሲሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሕወሓት ክልሉን እንደ ግል ኩባንያው ሲቆጣጠር መቆየቱን እና ለዚህ ይመቸው ዘንድ ሕዝቡን በየአካባቢው የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ሲከፋፍለው እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ አሠራር ከሕወሓት ውድቀት በኋላ ሊደገም እንደማይገባው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትግራይ የሁሉንም ሐሳብ የሚያስተናግድ ምቹ ሁኔታ የሚያስፈልጋት እንጂ የአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ርስት ልትሆን አትችልም ብለዋል።

በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚታየው ሁሉ በትግራይም ነፃነት እና ነፃ የሐሳብ ምርጫ መረጋገጥ እንዳለበት በመግለጽ፣ የሕዝቡን አንድነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

ሁሉም የአካባቢው ማኅበረሰብ በከባድ ጭቆና ውስጥ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደፊት ልማትና መልሶ ግንባታ በሚሠራበት ወቅት ሁሉም አካባቢዎች እኩል ትኩረት እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚኖረው የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም እንዲመለስ፣ የወደመውን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ለመጠገን እንዲነሳ፤ እንዲሁም በምርጫ ሕጋዊ አስተዳደር እስኪመሠረት ድረስ አንድነቱንና ተቋማቱን እንዲጠብቅ እና ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ታጣቂ ወጣቶች ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላም እጃቸውን በመስጠት ወደ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋም ሂደት እንዲገቡ ጠይቀዋል።

"ይበቃናል፣ የሚያዋጣው ሰላም ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታጣቂዎች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ፣ ወንጀል ያለባቸው በኢትዮጵያ ሕግ እንዲዳኙ፣ ነፃ የሆኑት ደግሞ በሀገራቸው በሰላም እንዲኖሩ መክረዋል።

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

 በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: