የአፍሪካ ነፃነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን ለክብራቸው እና ለማንነታቸው ባልተንበረከኩ ጀግኖች ከፍተኛ የተጋድሎ መሥዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ፣ ይህንን አባቶች ያቆዩልንን ነፃነት ለአዲሱ ትውልድ ወደ ተጨባጭ ዕድል የመለወጥ አደራ እንዳለብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ኤልዶሬት ከተማ በተከበረው የማሹጃ (የጀግኖች ቀን) በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ሰላምታ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸው፣ የኤልዶሬት ከተማ እና የኬንያ ሕዝብ ላደረጉላቸው ወንድማማችነታዊ አቀባበል እና እንግዳ ተቀባይነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ በጥቅምት 1952 (እ.አ.አ) በቅኝ ገዥዎች የተያዙት የኬንያ የነፃነት አባት ጆሞ ኬንያታ እና አምስቱ ባልደረቦቻቸው ታስረው የነበረበት ሁኔታ የትግሉ ተምሳሌት እንደነበር በማውሳት፣ ስማቸው ያልተወሳ በርካታ ኬንያውያን ያካሄዱት ተጋድሎ የአፍሪካውያንን ነፃነት ያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ የኬንያውያን የነፃነት ታሪክ ከኢትዮጵያውያን ታሪክ ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በ1896 (እ.አ.አ) በዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው ተምመው ሀገራቸውን በጋራ መከላከል መቻላቸውን አውስተዋል። የትግል ዓይነቱ ቢለያይም እምነቱ ግን አንድ እና እሱም “የአፍሪካውያንን የወደፊት ዕድል በራሳችን የመወሰን ጽኑ ፍላጎት» እንደነበር አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር ጀግኖች የነፃነት ታጋዮች ብቻ ሳይሆኑ መምህራን፣ ነርሶች፣ አርቲስቶ፣ አትሌቶች እና የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች ጭምር መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሀገራቸው ሲሉ የቆሰሉ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችንም በዚሁ ዕለት ማሰብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኤልዶሬት የጀግኖች እና የሻምፒዮኖች ከተማ መሆኗን በመጥቀስም፣ አትሌቶች ለስኬት ለመብቃት ዓመታትን እንደሚደክሙ፣ አሰልጣኝ እና ደጋፊ ማኅበረሰብ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ፣ ሀገርንም ለመገንባት ጽናት፣ ሰላምን የመጠበቅ ጀግንነት፣ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን የመገንባት ትዕግሥት እና በወጣቶች ላይ እምነት ማደር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአዲሱ ወጣት ትውልድ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ነፃነት አደራ መሆኑን እና ይህንን አደራ ወደ ሥራ፣ ዕድገት እና የተሻለ ሕይወት የመለወጥ ኃላፊነት የወጣቶች መሆኑን በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ከኬንያ ጎን እንደምትቆም አረጋግጠዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: