የኑክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀም የሀገራችንን የኃይል ዋስትና በማጠናከር እየገሰገሰ ያለውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሠረታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ራዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለውን የኢትዮጵያ ኑክሌር ኃይል ኮሚሽን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልዕቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ የምትታወቅ ሲሆን፣ አዲሱ የሀገራችን የዕድገት ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና የጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኮረ ነው።
አስተማማኝ እና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማት እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ኑክሌር ኃይል ኮሚሽን ለብሔራዊ የኑክሌር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ረገድ ስትራቴጂካዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አያይዘውም ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋት እና የተቋሙን ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ ተግባራት መሆናቸውን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በማዳበር የኑክሌር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን እንደሚያስችል አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: