በትግራይ ክልል አስገዳጅ ከሆነው የጦርነት ቀጣና ተላቆ በራሱ ፈቃድ ወደ ሰላም አማራጭ የገባው ወጣት የተሃድሶ ሥልጠና ወስዶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲቀላቀል እየተሠራ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ እንዳስታወቁት በግድ ወደ ጦርነት የገቡ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ታጣቂዎች ከነበሩበት አደረጃጀት በመውጣት በራሳቸው ፈቃድ ወደ ሰላም አማራጭ ገብተዋል።
ወጣቶቹ የተሰጣቸውን የሰላም እድል ተጠቅመው በየአካባቢው በተዘጋጁ የዲዲአር (DDR - ትጥቅ ማስፈታት፣ ከውትድርና ማሰናበት እና ወደ ሕብረተሰቡ የመቀላቀል) ማዕከላት እንዲመዘገቡ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በመቐለ ማዕከል እስካሁን ድረስ ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበዋል።
በሽሬ ማዕከል ከ3 ሺህ በላይ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፣ በዓዲግራት፣ በማይጨው እና በሌሎች አካባቢዎችም በርካታ ቁጥር ያላቸው የቀድሞ ታጣቂዎች በስፋት እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት በአሁኑ ወቅት ሰፊ ማብራሪያና ማስገንዘቢያ የሚሰጥበት የቅድመ-ዲዲአር (Pre-DDR) ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል።
ወጣቶቹ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ሲመለሱ በእጃቸው የሚገኘውን ማንኛውንም የጦር መሣሪያና ወታደራዊ ቁሳቁስ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አስረክበው መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ህጋዊ መታወቂያቸውን በመያዝ ከፊታችን ሀሙስ ጀምሮ ለአንድ ወር ወደተዘጋጁት የተሃድሶ ማዕከላት ገብተው የተሃድሶ ሥልጠና እና ሙሉ የዲዲአር ሂደት እንደሚከታተሉ ብርጋዴር ጄኔራል ደሪቤ መኩሪያ ገልጸዋል።
ይህ የሰላምና የተሃድሶ እመርታ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ በሰላምና በይቅርታ የተራመደ #ትልቅሕዝብ እና ለዘላቂ አገራዊ አንድነት የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር የሚያረጋገጥ ነው።
የትግራይ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ ማኅበረሰብ የመቀላቀል ሂደት የሀገራችንን ሰላምና ልማት ይበልጥ የሚያጠናክር ታሪካዊ እርምጃ ሆኖ ይቀጥላል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: