“መልክዓ ምድር ጎረቤት አደረገን፤ ታሪክ ወንድማማች አደረገን፤ ምርጫችን ደግሞ የጋራ ብልጽግና አጋሮች ሊያደርገን ይገባል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ኤልዶሬት ከተማ በተከበረው “ማሹጃ” (የጀግኖች ቀን) በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በስፖርት መድረክ በፉክክር ቢሮጡም፣ የጋራ ሀገሮቻቸውን፣ ሕዝቦቻቸውን እና አህጉራቸውን በመገንባት በኩል አስተማማኝ እና ጠንካራ የልማት አጋሮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በተፈጥሯዊ አቀማመጣቸው የማይነጠሉ ጎረቤቶች፣ በታሪክ አጋጣሚያቸው ደግሞ የጠበቀ ወንድማማችነት ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ይህ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ትሥሥር ወደ ላቀ የጋራ ብልጽግና እና ዘላቂ ወዳጅነት መለወጥ እንዳለበት እና የሁለቱ ሀገራት መሪዎች እና ሕዝቦች ምርጫ የጋራ ዕድገት መሆን እንደሚገባው አስምረውበታል።
የሁለቱ ሀገራት አትሌቶች በመሮጫ ሜዳዎች ላይ ጎን ለጎን እየሮጡ አንዳንዴ ኬንያ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ እያሸነፈች በዓለም መድረክ የአፍሪካን ታላቅነት እና ልዕልና ማሳየታቸውን አውስተዋል።
ይህ በውድድር የመፎካከር እና በልማት ደግሞ በጋራ የመገንባት መንፈስ በኢትዮጵያ ‘መደመር’ ከሚለው እሴት ጋር የሚጣጣም እና አቅሞችን ለጋራ ዓላማ ማስተባበር መሆኑን አስረድተዋል።
በተግባር የተረጋገጠ የልማት እና የመሠረተ ልማት ትሥሥር
ከእ.አ.አ 2022 ጀምሮ በድንበር ተሻጋሪ የኃይል መስመር ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚላከው ንጹሕ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያውያን መኖሪያ ቤቶች ብርሃንን፣ ለኢንዱስትሪዎች ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጉልበትን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ከሞምባሳ ወደ ሐዋሳ የተዘረጋው ዘመናዊ የትራንስፖርት ኮሪደር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የሕዝብ ለሕዝብ እንቅስቃሴ እያፋጠነው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ የተሰማራው ሳፋሪኮም ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ከማገናኘቱም በላይ፣ የኤም-ፔሳ (M-Pesa) አገልግሎት የገንዘብ ዝውውር እና የክፍያ ሥርዓቱን በማቀላጠፍ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትሥሥር ማሳደጉን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት አሁን ካሉበት የትብብር ደረጃ ይበልጥ ወደፊት መጓዝ እንዳለባቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አርሶ አደሮች እና አምራቾች በድንበር ላይ በነፃነት እና በቀላሉ እንዲነግዱ፣ ሕዝቦች እርስ በእርስ እንዲጎበኙ፣ ባህላቸውን እንዲያውቁ እና አብረው እንዲማሩ፣ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት የበርካታ ቤተሰቦችን ሕይወት በቀጥታ እንዲለውጥ ትብብሩ በሁሉም ዘርፍ ይበልጥ ሊፋጠን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: