Search

የትግራይ ህዝብ ጦርነት አንገሽግሾታል፤ ሰላምና ልማት ናፍቆታል":- ብ/ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር)

ማክሰኞ ጥቅምት 10, 2019 84

የትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታ እና ሰላም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር) ከኢቲቪ (ETV) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የትግራይ ህዝብ ተደጋጋሚ ጦርነት ስለሰለቸው አሁን ላይ ሰላምና ልማትን በጽኑ እንደሚፈልግ ገለጹ።

እንደ ብርጋዴር ጄኔራሉ ገለጻ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ውጊያውን ቢያቆመውም ህገ ወጡ ህወሓት ለዳግም ጦርነት ሲዘጋጅ በመቆየቱ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ፈቃደኛ አልነበረም።

በዚህም ምክንያት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ህይወት የማመለስ (DDR) ሂደት በጥርጣሬ ታይቶ ሳይተገበር በመቅረቱ ወጣቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ህገ ወጡ ህወሓት ወጣቱን ወደ ሌላ ወታደራዊ ግጭት በመክተቱ ክልሉ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት መዳረጉን ያመላከቱት ሥራ አስፈጻሚው፤ በአሁኑ ወቅት ክልሉ በርካታ ቁስለኛ፣ ተፈናቃይ እና የትምህርት እድል ያጡ ወጣቶች የበዙበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ትጥቅ የማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም (DDR) መርሃ ግብር ለዘላቂ ሰላም፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ወጣቶች በህጋዊ መንገድ ሰርተው እንዲያልፍላቸው ፍጹም አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር፤ አሁንም በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ጊዜያቸውን በውትድርና ሳያባክኑ በወጣትነት እድሜያቸው ወደ ሰላማዊ መንገድ መጥተው ህይወታቸውን እንዲያስተካክሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ክልሉን ሲያምስ የነበረው ቡድን የትግራይን ህዝብ የማይወክል፣ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ክልሉ እንዲወድም ከሚፈልገው ሻዕቢያ ጋር የተቀናጀ እና ሀብት የዘረፈ ቡድን መሆኑ ተጋልጧል ብለዋል።

አሁን ላይ ወጣቱም ሆነ ህዝቡ ጦርነት የማይፈልግ በመሆኑ ቡድኑ በኃይል አሸንፋለሁ ማለቱ የቅዥት ያህል እንደሆነ እና ህዝቡም ከጎኑ እንደሌለ አክለው ገልጸዋል።

ይህ የህዝቡ የሰላም ፍላጎትና ተጋላጭነትን የማቆም ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ በሰላምና በልማት ጎዳና ላይ የተራመደ #ትልቅሕዝብ እና ለቀጣናዊ ብልጽግና የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር የሚያስመሰክር ታሪካዊ እውነት ነው።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: