"መልህቅ ዓርማዬ፣ ቀይ ባሕር ቤቴ"
"መልህቅ ዓርማዬ፣ ቀይ ባሕር ቤቴ፣
የጀግንነት ውርሴ፣ የአባት የአያቴ"
የሚለው ታሪካዊ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መዝሙር፣ የነፃነት፣ የሉዓላዊነት እና የሺህ ዓመታት የባሕር ላይ የበላይነት መገለጫ በመሆን ለትውልዶች ሲዘመር የኖረ ሕያው ማኅተም ነው።
ኢትዮጵያ ትላንት በጂኦፖለቲካዊ ሴራዎች፣ በፖለቲካዊ ግድየለሽነት እና በታሪካዊ ስህተቶች የባሕር በሯን እንድታጣ መደረጓ፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ ለወደብ ኪራይ ውድ ወጪ እና ለስትራቴጂካዊ ስጋቶች አጋልጧታል።
ይሁን እንጂ ዛሬ የመደመር መንግሥት በጀመረው ጽኑ ሀገራዊ ጥረት እና ቁርጠኝነት፣ ኢትዮጵያ ዳግም የባሕር በሯን በማስመለስ ቀደምት ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ገፅታዋን እንደምትመልስ ትልቅ ተስፋ ተሰንቋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባል ፒቲ ኦፊሰር ያዕቆብ ጳውሎስ ከኢቲቪ መዝናኛ ጋር ባደረጉት ቁምነገር አዘል ቆይታ፣ ይህንኑ የታሪክ ጠባሳ፣ የሀገር ፍቅር ናፍቆት እና የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ በቁጭትና በደስታ ተረክዋል።
ኢትዮጵያ በወቅቱ በጠንካራ ወታደራዊ መዋቅር እና በዘመናዊ የጦር መርከቦች የታነፀ ስመ-ጥር የባሕር ኃይል እንደነበራት የሚያስታውሱት ፒቲ ኦፊሰር ያዕቆብ፤ በ1975 ዓ.ም. አዲግራት አካባቢ ይታዩ የነበሩትን የባሕር ኃይል አባላት ግርማ ሞገስ እና ንጽህና ተመልክተው ከልጅነታቸው ጀምሮ በፍቅር እንደተሳቡ ይናገራሉ።
በወቅቱ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የነበረው ከፍተኛ ውድድር አልፈው ወደ አሰብ ማሰልጠኛ ማዕከል በመግባት በ"1038" ታንክ እና ጦር አጓጓዥ መርከብ ላይ ተመድበው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ይሁን እንጂ በ1983 ዓ.ም. በነበረው የፖለቲካ ሴራ የባሕር ኃይሉ እንዲበተን እና ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንድታጣ ሲደረግ፣ የደረሰው ታሪካዊ ጉዳት በግል ሕይወታቸው ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይ ከባድ ፈተና ጥሎ አልፏል።
በወቅቱ በተፈጠረው ግርግር እና የወታደራዊ መዋቅሩ መፍረስ ምክንያት ከእጮኛቸው ጋር ተለያይተው የቆዩ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ከስደት ተመልሰው ከባለቤታቸው ጋር ኑሮ ቢጀምሩም በፖለቲካው ሴራ ምክንያት ንብረታቸውን በሙሉ ጥለው ለመውጣት ተገደዋል፤ ይህም የቀይ ባሕር ማጣት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እንዴት እንደበተነ በቁጭት ያስታውሳሉ።
የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያስገነዘቡት የቀድሞው መርከበኛ፤ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ወረራዎችን በሙሉ ያስተናገደችው በባሕር በኩል በመሆኑ፣ ሀገርን በባሕር፣ በምድር እና በአየር ለመጠበቅ የሰለጠነ የባሕር ኃይል እና የማሪን ኮማንዶ መዋቅር አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ።
ትላንት በሴራ እና በስህተት ያጣነውን የባሕር በር ዛሬ የመደመር መንግሥት "ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል፣ ይሄ ውልፍት የማይል አቋማችን ነው" በሚል የያዘውን ጽኑ የዲፕሎማሲ እና የስትራቴጂ እንቅስቃሴ ሲሰሙ ትልቅ ተስፋ እና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
"ዓባይ ግድብ ላይ ያሳካነውን ታሪካዊ ድል በቀይ ባሕርም ላይ እንደምናሳካው ሙሉ እምነት አለኝ፤ ቀይ ባሕር ሲከፈት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ብዙ ኢትዮጵያውያን ቤታቸውን ጥለው የመጡ አሉ፤ ከዚህ የበለጠ ምን ደስታ ይገኛል? ወደ ቤቴ ስለምገባ በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው የምሄደው፤ ለባሕር ኃይሉም ባለኝ አቅም ሁልጊዜም ድጋፍ አደርጋለሁ" ሲሉ ፒቲ ኦፊሰር ያዕቆብ ተናግረዋል።
ቀይ ባሕር ላይ መዋኘት እንደናፈቃቸው የተናገሩት የቀድሞው መርከበኛ፤ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ዳግም መቋቋሙ እና ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ለትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ብሔራዊ አደራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: