በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመደመር ፍልስፍና በመነጨ አስተሳሰብ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ ሀገራችንን በሚገባት ከፍታ ላይ የሚያስቀምጡ እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አለቃው ከበደ (ዶ/ር) ከኢቲቪ 57 ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በፋይናንስም ሆነ በቴክኖሎጂ አቅም ይታሰባሉ ተብለው የማይገመቱ ህልም መሰል ፕሮጀክቶች ዛሬ በመሬት ላይ ተግባራዊ መሆናቸው የሀገርን ከፍተኛ የመፈጸም አቅም ያበሰረ ነው።
ፕሮጀክቶቹ በጠንካራ ክትትል፣ በከፍተኛ የሥራ ዲሲፕሊንና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በጀት መጠናቀቃቸው የመንግሥትን የተግባር አቅም ማሳየቱንም አብራርተዋል።
እንደምሁራኑ ገለጻ ፕሮጀክቶቹ በራስ አቅም መከናወናቸው የፖሊሲ ነፃነትን የሚያረጋግጡና ለኢኮኖሚ ሽግግር መደላደል የሚፈጥሩ ናቸው።
እንደ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው።
ፈጠራና ፍጥነት ታክሎባቸው እየተከናወኑ ያሉት ፕሮጀክቶች፣ ከተሞችን ከገጠር የሚያገናኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የኮሪደር ልማቶች በከተማ እና ገጠር መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠቡ ናቸው።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዱጋሳ አበባ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ምርታማነትን በመጨመር የገቢ ንግድን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያስችላሉ።
ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትን ከመቀነሱም በላይ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ያመጣል።
በአጠቃላይ እነዚህ አዳዲስ አሠራሮች እና የኮሪደር ልማቶች ኢትዮጵያውያን "መሥራት እንችላለን" የሚል የሥነ-ልቦና ዝግጅትና አዲስ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ማድረጋቸውን እና የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ጉዞ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ምሁራኑ አብራርተዋል።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: