Search

"የጣና ፎረም ለአፍሪካ ሰላም እና ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው"፦ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ቅዳሜ ጥቅምት 14, 2019 53

ሰላማዊ፣ ጽኑ እና የበለጸገች የአፍሪካ አህጉርን ለመገንባት የጣና ፎረም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

በ12ኛው የጣና ከፍተኛ የደኅንነት ፎረም ላይ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጣና ሐይቅ እና የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችው ባሕር ዳር ከተማ አስደናቂ ተፈጥሯዊ ውበት፣ ጥልቅ ባህላዊ ቅርሶች እና ረጅም የዕውቀት ባህልን አጣምራ የያዘች በመሆኗ ለንደዚህ አይነት መድረኮች ተስማሚ መሆኗን ተናግረዋል።

ከተማዋ በዩኔስኮ የዕውቀትና የመማሪያ ከተማነት እውቅና እንዳላት የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም ልምዶች የሚካፈሉበት፣ ሐሳቦች የሚፈተኑበት እና አዳዲስ የመፍትሔ መንገዶች የሚታሰቡበትን ፎረም ለማስተናገድ ልዩና ብቁ ያደርጋታል ብለዋል።

አክለውም ባሕር ዳርን በኮንፈረንስ ማዕከልነቷ ብቻ ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት አቅሟ ይበልጥ ለማጠናከር እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጣና ፎረምን በማስተናገዱ ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማው የገለጹት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ ወደፊትም ይህንን ግንኙነት በከፍተኛ የእንግዳ ተቀባይነት፣ የዝግጅት እና የአጋርነት ደረጃዎች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አክለውም ከፌዴራል መንግሥት፣ ከፎረሙ አመራር እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባሕር ዳር ደኅንነቷ የተጠበቀ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ብቁ መኖሪያ ሆና እንድትቀጥል ጥረቱ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።

የጣና ፎረም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ባሕር ዳርን ለአፍሪካውያን ግልጽ ውይይት እና ለጋራ ፈተናዎች አፍሪካ መራሽ መፍትሔዎችን መፈለጊያ ሥፍራ ማድረጉን ያነሱት አቶ አረጋ፤ ፎረሙ አመራርን ከአስተሳሰብ፣ ልምድን ከማስረጃ፣ እንዲሁም የሰላም ፍለጋን ከሕዝብ ምኞት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ የውይይት ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የክልሉ መንግሥት ደኅንነት እና ልማት የማይለያዩ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ዘላቂ ደኅንነት የሚረጋገጠው በልማት ዕድሎች፣ በአካታችነት፣ በፍትሕ እና በድንበሮች መካከል በሚደረግ የጋራ ትብብር መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: