የጣና ፎረም በጥልቅ ለማሰብ፣ ለስትራቴጂካዊ በጎ እይታ እና ለአህጉሪቱ ሉዓላዊ መፍትሔዎችን ለማመንጨት ግልጽና እውነተኛ የአፍሪካ ቦታ መሆኑን የጋና ፕሬዝደንት እና የጣና ፎረም ቦርድ ሊቀመንበር ጆን ድራማኒ ማሃማ ገለጹ።
በባሕር ዳር ከተማ በተጀመረው 12ኛው የጣና ከፍተኛ ደረጃ የደኅንነት ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጣና ፎረም ከተለመዱት አስገዳጅ ዲፕሎማሲያዊ ሥነ-ሥርዓቶች ወጥቶ ስለ አህጉሪቱ ሰላም፣ አስተዳደር እና ደኅንነት የህልውና ጉዳዮች በጥልቀት ለመመከር የሚያስችል ልዩ መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።
መሠረታዊውን አህጉራዊ እውነት ያብራሩት ፕሬዝደንቱ፤ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ሊገነባ የሚችለው በአፍሪካውያን ባለቤትነት እና በእውነተኛ የሕይወት እውነታዎች ላይ ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ስብሰባው በጋራ ጥበብ እና በሞራል ኃላፊነት የተመሠረተውን የጣና መንፈስ እንደሚያንጸባርቅ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ሥር ነቀል ለውጥ እያስተናገዱ መሆኑን ያመለከቱት ሊቀመንበሩ፤ የተካረረ የጂኦፖለቲካ ውድድር፣ ለስትራቴጂካዊ ማዕድናት የሚደረግ ሽኩቻ፣ የዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መዛባት እና የቴክኖሎጂ መረበሾች የዓለም አቀፉን ሥርዓት እንደገና እያበጁት እንደሆነ አብራርተዋል።
በዚህ በተከፋፈለ የዓለም ሁኔታ ውስጥ አፍሪካ ዝም ብላ ተመልካች መሆን እንደሌለባትና አህጉሪቱ የውጭ ኃይሎች የፉክክር ሜዳ እንድትሆን መፈቀድ እንደሌለበባት አሳስበዋል።
ወደ ገበያ የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች እንዳሉ የሚገልጽ የእስያ-አፍሪካ ምሳሌ በመጥቀስ፣ ይህም አንድን ችግር ለመፍታት በርካታ አማራጮች እንዳሉ የሚያሳይ መሆኑን ፕሬዝደንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ገልጸዋል።
ሰላም የመጨረሻ ግባችን ከሆነ፣ የአፍሪካ ልዩ ልዩ ተሞክሮዎች፣ ተቋማዊ ፍላጎቶች እና የሕዝብ ቁጥር ጥንካሬ ወደዚያ ግብ ለመድረስ በርካታ መንገዶችን እንደሚሰጡን በመግለጽ ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: